የብሪክስ (BRICS) ትብብር ማዕቀፍ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች የበለጠ ውክልና ለማግኘት፣ የኢኮኖሚ አጋርነቶችን ለማስፋትና ለዘላቂ ልማት አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር ለሚፈልጉ ታዳጊ አገሮች የሚሰጠው ጠቀሜታው እየጨረ ነው።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነቷ የንግድ ግንኙነቶችን ለማጠናከር፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ለማስፋፋትና ከታዳጊ ኢኮኖሚዎች ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ይጠቅማታል።
በቻይና በሚካሄደው በመጭው የብሪክስ ጉባኤ፣ አባል አገራቱ የበለጠ አካታች የዓለም አቀፍ ሥርዓትን ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደገና እንደሚያረጋግጡና በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የልማት ተግዳሮቶች ላይ ተግባራዊ መፍትሔዎችን እንደሚያፈላልጉ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሏል።
የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ፍጹም ግርማ
“መጪው ጉባኤ ብሪክስ የበለጠ ፍትሐዊና እኩልነትን ያረጋገጠ የዓለም ሥርዓት ለመገንባት ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥበት አበረታች ክስተት ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ” ብሏል።
ፍጹም አክሎም እንደገለጸው ብሪክስ የኢኮኖሚ ትብብርን በማጠናከርና ታዳጊ ኢኮኖሚዎች በዓለም አቀፍ ውሳኔ አሰጣጥ የበለጠ ድምፅ እንዲኖራቸው በማድረግ፣ አፍሪካን ጨምሮ ለሰፊው የዓለም ደቡባዊው ክፍል አስፈላጊ ዕድሎችን የሚፈጥር ነው።
ቻይና በእነዚህ ጥረቶች ውስጥ ያላት ሚና እጅግ ወሳኝ ነው።
ፍጹም “ቻይና ከብሪክስ መመሥረት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዚህ የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ መሪ ሚና እየተጫወተች ነው። ማዕቀፉን በማጠናከር ረገድም ያላት ሚና ወሳኝ እንደነበር አምናለሁ” ሲሉ ተናግሯል። በተጨማሪም ቻይና በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በአቅርቦት ሰንሰለት ትብብርና በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ ላይ ባቀረበቻቸው ሐሳቦች ለትብብሩ እድገት አስተዋጽኦ ማድረጓን ጠቅሷል ፍጹም።
የብሪክስ አባልነት ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድን ለማስፋፋት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የልማት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች ለማስፈጸም ተጨማሪ ዕድሎችን ሊከፍት ይችላል። ፍጹም እንዳለው ብሪክስ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው የልማት ጉዳዮች ጋር በተሻለ ሁኔታ የሚጣጣሙ እጅግ ብዙ ዕድሎችን ያቀርባል። ይህም አዳዲስ ገበያዎችን ማግኘትን፣ የኢንቨስትመንት አጋርነቶችን ማስፋፋትንና እንደ አዲሱ የልማት ባንክ (New Development Bank) ባሉ ተቋማት በኩል የልማት ፋይናንስ ማግኘትን ያካትታል።
ከብሪክስ የሚገኙ ጥቅሞች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይወሰኑ በመላው አፍሪካ ሊስፋፉ የሚችሉ ናቸው። በመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በክህሎት ልማት አማካኝነት፣ የብሪክስ ትብብር የአፍሪካ አገራት ድንበር ተሻጋሪ ንግድን እንዲያጠናክሩና በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለቶች ውስጥ የበለጠ ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሊረዳ ይችላል።
ፍጹም “የአፍሪካን ገበያዎች ከዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለቶች ጋር በማገናኘት ረገድ፣ ቻይና በሁለት መንገዶች የራሷን ሚና መወጣት ትችላለች ብዬ አምናለሁ” ብሏል። የኢኮኖሚ ባለሙያው ፍጹም እንደተናገረው አንደኛው የአፍሪካን የምርት አቅም ከዓለም አቀፍ የግዥና የአቅርቦት ሥርዓቶች ጋር ማቀናጀት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አገራት በጥሬ እቃዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ እሴት ጨምረው ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ ድጋፍ ማድረግ ነው።
ፍጹም የብሪክስ ስኬት የሚለካው ትብብሩን ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ውጤቶች ሲቀየር ነው ብሏል። ለኢትዮጵያና ለሰፊው የዓለም ደቡባዊው ክፍል፣ ዋናው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እየጨመረ የመጣውን ዓለም አቀፍ አጋርነት ወደ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት፣ ወደ ጠንካራ ኢንዱስትሪዎች፣ ወደ ሰፊ የገበያ ተደራሽነትና ሁሉን አሳታፊ ወደሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት መቀየር ይሆናል።

ቻይና፣ ብሪክስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ ሀገራት የሚሰጠውን ድጋፍ የበለጠ በማጠናከር ወሳኝ ሚና ያላት የዓለም ሁለተኛ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገር ነች። ሀገሪቱ በዚህ አመት ይፋ ባደረገችው የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲዋ 53 የአፍሪካ ሀገራት ምርቶቻቸውን ወደሰፊው የቻይና ገበያ ያለ ታሪፍ እንዲልኩ እድሉ የተመቻቸላቸው ሲሆን ይህን ተከትሎም የአፍሪካ-ቻይና የንግድ ልውውጥ መጠን ጨምሯል።













