Loading...

በኬንያ 190 ህጻናት ተገደው እንዲጾሙና አንዲሞቱ አድርጓል የተባለው የኑፋቄ መሪ በፍርድቤት ጥፋተኛ ተባለ

Kenyan court convicts cult leader over deaths of nearly 200 children

የኬንያ ፍርድ ቤት 190 ህጻናትና አንድ ጎልማሳ ተገደው እንዲጾሙ በማድረግ እንዲሞቱ አድርገዋል ባላቸው የኑፋቄ ስብከት መሪው(cult leader) ማኬንዚንና ሌሎች 28 ተከሳሾችን በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ሲል ወስኗል።

ማኬንዚ እ.ኤ.አ. በ2023 ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ ተይዘው ነበር። ከዚያም በኬንያ ደቡብ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኘው የሻካሆላ ደን ውስጥ በጥልቀት ባልተቆፈሩ መቃብሮች ውስጥ አስከሬኖች መገኘት ጀመሩ።

አቃቤ ሕጎች እንደገለጹት ማኬንዚና የሚመራው “የጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል ቤተ ክርስቲያን” የዓለም ፍጻሜ እንደሚመጣ የሚያምን የክርስቲያን ኑፋቄ አደራጅቶ ነበር። ተከታዮቹም ዓለም ከማብቃቷ በፊት ወደ ሰማይ ለመግባት ሲሉ ራሳቸውንና ልጆቻቸውን በረሃብ እንዲያስጨርሱ ያዝ እንደነበር አቃቤ ሕጎች ገልጸዋል።

ጉዳዩ በሻካሆላ ደን ውስጥ የጅምላ መቃብሮች ከተገኙበት ጊዜ ጀምሮ የኬንያን ሕዝብ ትኩረት ስቧል። ማኬንዚ ከዚህ ቀደምም በባለሥልጣናት ክትትል ሥር እያለ እንዴት ሥራውን መቀጠል እንደቻለ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ፖሊስ እአአ በ2017 ግቢውን ፈትሾ እንደነበር ተገልጿል።እአአ በ2019 ባለሥልጣናት ቤተ ክርስቲያኑን ከዘጉ በኋላ ማኬንዚ ወደ ሻካሆላ ደን መሄዱን ፖሊስ ገልጿል።

ሰለባዎች የፍርድ ውሳኔውን አወደሱ

ማኬንዚ የግድያ ክሶቹን በመካድ ተጎጂዎቹን በረሃብ እንዲሞቱ አላስገደድኳቸውም ብሏል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ የቀረበውን መከላከያ ውድቅ አድርጓል።

ማኬንዚና ሌሎች ጥፋተኛ የተባሉት ተከሳሾች በሶስት ሳምንታት በኋላ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል። ማኬንዚንና ከሌሎቹ ተከሳሾች አብዛኞቹን የሚወክለው ጠበቃ ላውረንስ ኦቦንዮ ደንበኞቹ ይግባኝ እንዲጠይቅ እንዳዘዙት ገልጿል።

በኑፋቄው ምክንያት ስምንት የቤተሰብ አባላቱንና ሁለት የልጅ ልጆቹን ያጡት የ62 ዓመቱ ፍራንሲስ ዋንጄ የፍርድ ውሳኔውን በደስታ ተቀብለዋል። ውሳኔው በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያላቸውን እምነት እንዳጠናከረላቸው ለሮይተርስ ተናግረዋል።

“በዛሬው ውሳኔ ከተከሰተው ብዙዎች ትምህርት ይወስዳሉ” ያሉት ዋንጄ፣ ሕዝቡ የሚያገኛቸውን የሃይማኖት ተቋማት በጥንቃቄ መመልከት እንዳለበት አሳስበዋል።

ከ400 በላይ አስከሬኖች ተገኝተዋል

በሻካሆላ ደን ውስጥ በአጠቃላይ ከ400 በላይ አስከሬኖች ተገኝተዋል። ከሕፃናቱ አስከሬኖች ብዙዎቹ በከፍተኛ ሁኔታ በመበስበሳቸው እስካሁን 26ቱን ብቻ ነው መለየት የተቻለው። ከሌሎቹ ሞቶች ጋር የተያያዙ ምርመራዎችም ቀጥለዋል።

ዳኛ ዲያና ካቬድዛ ሞቻቼ ከስምንት ሰዓታት በላይ በቆየው የችሎት ሂደት፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ሕፃናት ከሌሎች ተለይተው ምግብ እንዳያገኙ ሲደረግ ወላጆቻቸው ይመለከቱ እንደነበር ገልጸዋል።

ከውሳኔው በኋላ በሞምባሳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለጋዜጠኞች የተናገሩት የኬንያ የሕዝብ አቃቤ ሕግ ዳይሬክተር ሬንሰን ኢንጎንጋ፣ “ይህ ከሁሉም የተሻለ ውሳኔ ነው” ብለዋል።

ማኬንዚ በችሎቱ ላይ ባለመስመር ቲሸርትና ቀይ ሱሪ ለብሶ ከተከሳሾቹ መካከል ከሆነችው ሚስቱ አጠገብ ተቀምጦ ነበር።

ጉዳዩ በኬንያ በሃይማኖት ተቋማትና በሌሎች ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ላይ የበለጠ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ጥሪዎችን አስነስቷል። በአገሪቱ ሕዝባዊ ሕይወት ውስጥ ሃይማኖት ጉልህ ሚና ይጫወታል። የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እአአ በ2023 የመንግሥት ተቋማት ሞቶቹን መከላከል ይገባቸው እንደነበር በመግለጽ እንደ ፕሬዝዳንት ኃላፊነት እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

መጀመሪያ በረሃብ እንዲሞቱ የተደረጉት ህጻናት

ስለ ኑፋቄው እንቅስቃሴ ቀጥተኛ መረጃ ያላቸው ሰዎች ለሮይተርስ እንደገለጹት ማኬንዚ የጅምላ ረሃብ ዕቅዱን በሦስት ደረጃዎች አዘጋጅቶ ነበር። በመጀመሪያ ሕፃናት፣ ቀጥሎ ሴቶችና ወጣት ወንዶች፣ በመጨረሻም የቀሩት ወንዶች በረሃብ እንዲሞቱ ታቅዶ ነበር።

የቀድሞ የታክሲ ሹፌር የነበረው ማኬንዚ፣ የኑፋቄው አባላት ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት እንዳይልኩና ሲታመሙም ወደ ሆስፒታል እንዳይወስዷቸው ይከለክል እንደነበር የተጎጂዎች ዘመዶች ከዚህ በፊት መናገራቸውን ይታወሳል። እነዚህን ተቋማትም “የሰይጣን ሥራዎች” በማለት ይጠራቸው እንደነበር ተገልጿል።

የኑፋቄው አባላት በፕላስቲክ ሸራና በገለባ በተሠሩ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ይኖሩ ነበር። ማኬንዚም አካባቢዎቹን እንደ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ ባሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስሞች ከፋፍሎ ነበር።

የተከታዮቹ ሁኔታ ለሕዝብ ይፋ መሆን የጀመረው እአአ በመጋቢት 2023 አካባቢ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ወንድሙና ሚስቱ በማኬንዚ ትዕዛዝ ልጆቻቸውን በደኑ ውስጥ በረሃብ እንዳስጨረሱ ለፖሊስ ሪፖርት ካደረገ በኋላ ነው።

ማኬንዚ በመጀመሪያ ቢታሰርም በዋስ ተለቋል። ፖሊስ እአአ በሚያዝያ 2023 እንደገና ካሰረው በኋላ ደኑን በስፋት መፈተሽና የጅምላ መቃብሮችን ማስቆፈር ጀመረ።

ማኬንዚ ከደኑ ውስጥ ከተገኙት ሞቶች ጋር በተያያዘ የሽብርተኝነት ክሶችን ጨምሮ ሌሎች ክሶችም ቀርበውበታል። እነዚህን ክሶች ግን ክዷል።

አቃቤ ሕጎች እንደሚሉት ማኬንዚ በእስር ላይ እያለ ከሻካሆላ ደን 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኘው በኳ ቢንዛሮ መንደር ውስጥ የ52 ሰዎችን ሞት መርቷል። ማኬንዚ ግን በዚህ ጉዳይ የቀረበበትን ክስ አልተቀበለም።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው