ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በሁርሶ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት የፌደራል መንግስት ጦር ከህወሓት ጋር በድጋሚ ባደረገው ጦርነት የትግራይ የክልል ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን ከተቆጣጠረና ክልሉን ለስድስት ወራት የሚመራ ባለአደራ አስተዳደር ካቋቋመ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጠና ልብስ ከለበሱ ሰልጣኝ ባለስልጣናት ፊት ለፊት ሆነው ስፖርት ሲያሰሩና አብረው ቁጭ ብለው ሲወያዩ የሚያሳዩ ምስሎችን በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው አጋርተዋል።
ወታደራዊ ስልጠናው አመራሩ “በአካል የዳበረ፣ በሞራል የጠነከረ፣ በእውነት የተሳለ” እንዲሆንና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማምጣት እንዲሰራ እንደሚጠቅም የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የወታደራዊ ሳይንስ ስልጠና ኃላፊነትን በብቃት ለመፈጸም፣ በአርበኝነት መንፈስ አገልግሎት ለመስጠትና የጋራ ግብን ለማሳካት ያለውን አስፈላጊነት አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከዓመታት በፊት አምጸዋል የተባሉ ወታደሮችን ቤተመንግሥት ቅጥር ግቢ ውስጥ ስፖርት (ፑሽ-አፕ) ሲያሰሩ መታየታቸው ይታወሳል።











