ለቻይና-አፍሪካ ግንኙነት ጠንካራ መሰረት የጣለው የታዛራ ፕሮጀክት 50 አመት ሞላው

China Financed Tanzania-Zambia railway (TAZARA) turns 50 years

ለቻይና-አፍሪካ ግንኙነት ጠንካራ መሰረት በመጣል በጉልህ ከሚጠቀሱት ምልክቶች መካከል አንዱ የሆነው የታንዛኒያ-ዛምቢያ የባቡር ፕሮጀክት(ታዛራ) ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በዚህ ወር  ግማሽ ምዕተ-አመት ይሞላዋል። ከአምት አመት ግንባታ በኋላ እአአ በ1976 የተጠናቀቀው ፕሮጀክቱ ቀጣናዊ ትስስርን የቀየረና በደቡብ-ደቡብ (South-South) ትብብር በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው።

ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላም ታዛራ ከመጓጓዣ ኮሪደርነት ያለፈ ትርጉም አለው፤ የኢኮኖሚ የሕይወት መስመርና ዘመናዊው የቻይና–አፍሪካ ግንኙነት የተገነባበት መሠረት ሆኖ ቀጥሏል 

1860 ኪሎሜትር የሚረዝመውና የታንዛኒያዋን የዳሬ ሳላም ወደብ ከዛምቢያዋ ካፒሪ ሞፕሺ የሚያስተሳስረው ይህ የባቡር መስመር ግንባታ የተጀመረው እአአ በ1970 ነበር። ይህ ፕሮጀክት እውን መሆን ለውጭ ንግድ በአብዛኛው በወቅቱ በቅኝ ገዥዎች ወይም በአናሳዎች ቁጥጥር ስር ባለ ግዛት ጥገኛ ሆና ለነበረችው ዛምቢያ እረፍት የሰጠ ነበር። ይህ መስመር ሀገሪቱ ወደ ባህር ለመውጣት አማራጭ ከመሆንና የኢኮኖሚ ተጋላጭነትን ከመቀነስ ባሻገር፣ በቀጣናው ለነበረውን የነጻነት ትግል አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይነገራል።

ፕሮጀክት የተገነባው ከቻይና መንግስት ከወለድ ነጻ በተገኘ 406 ሚሊየን ዶላር ነው። በአፍሪካ ውስጥ ግዙፍ በሆነው በዚህ የመሰረተልማት ኢንቨስትመንት በሺዎች የሚቆጠሩ  ቻይናውን መሀንዲሶችና ሰራተኞች በአስርሺዎች ከሚቆጠሩ የታንዛኒያና ዛምቢያ ዜጎች ጋር በመሆን መስመሩን በአስቸጋሪ መልካምድር፣ ተራሮችን በማቋረጥ፣ በሸለቆዎችና በመቶዎች በሚቆጠሩ ድልድዮችና ቱቦዎች ላይ መስመሩን ዘርግተዋል። ታንዛኒያና ዛምቢያም በስምምነቱ መሰረት ብድራቸውን በመክፈላቸው ታዛራ የቻይና-አፍሪካ የቆየ ስኬታማ የፋይናንስ ትብብር ማሳያ ሆኗል።

ቻይና ለዚህ ፕሮጀክት ብደር የሰጠችው፣  ምዕራባውያን ሀገራት የተለመዱ መስፈርቶችን በማስቀመጥ ለማበደር ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ መሆኑ የአፍሪካን ልማት ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየችበት ነበር። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አብዛኞቹ ምዕራባውያን ሀገራት የባቡር መሰረተልማት ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት እንደሌለውና ለዚህ ኢንቨስትመንት ለማበደር ፍቃደኝነት እንደሌላቸው ይገልጹ ነበር። ነገርግን ቻይና ፕሮጀክቱን ከኢንቨስትመንት ይልቅ በታዳጊ ሀገራት መካከል የሚደረግ አጋርነት አድርጋ በመውሰድ ነበር ብድር የሰጠችው። ይህ በቻይናና በአፍሪካ ሀገራት መካከል መተማመን እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አድርጓል

የዚህ ፕሮጀክት ስኬት፣ ቻይና ከእዚያ ወዲህ  በአፍሪካ ለምታካሂዳቸው የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች መሰረት የጣለ ነው። በታዛራ ፕሮጀክት የተፈጠረው መተማመን፣ ቻይና በአሁኑ ወቅት በባቡር፣ በኢንዱሰትሪ ፓርኮች፣በመንገድ፣ በወደብና በመሳሰሉት ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንድትሰማራ አስችሏታል። ይህ ፕሮጀክት ቻይና ለአፍሪካ የልማት ትኩረቶች ምላሽ ከመስጠት ባሻገር ውስብስብ የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ስርቶ የማጠናቀቅ አቅም እንዳላት ያሳየችበትም ነው።

በዘመናዊ የቻይና-አፍሪካ ትብብር ከተሰሩት ግዙፍ የመሰረተልማት ፕሮጀክቶች መካከል ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ 759 ኪሎሜትር የዘረጋውና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራው የባቡር መስመር ተጠቃሽ ነው። በቻይና ተቋራጮችና ብድር የተገነባው ይህ ድንበር ተሻጋሪ መስመር፣ ወደ አልባ የሆነችውን ኢትዮጵያ የባህር ወደብ ካላት ጅቡቲ ጋር በማገናኘት የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ወሳኝ አበርክቶ አድርጓል። 

በመሆኑም ለዘመናዊ የአፍሪካ- ቻይና ትብብር መሰረት የጣለውን የታዛራ 50ኛ ዓመት ማክበር ፋይዳው ከብረት ሐዲዶችና ከባቡሮች ከፍ ያለ ነው። ፕሮጀክቱ መሰረተልማት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር አይነተኛ መሳሪያም ሊሆን እንደሚችል ያሳያል።

የቻይናና የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ዛሬ ካለበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ታዛራ በሁለቱ ወገኖች መካከል ለነበረው የልማት ትብብር፣ ፖለቲካ አጋርነት እና ስትራቴጂያዊ ግንኙነት እንደ ድልድይ ሆኖ አገልግሏል። ፕሮጀክቱ  በክልላዊ ትስስርም ሆነ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ላይ ጥልቅ ተፅዕኖ ካሳረፉ ጥቂት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ መሆን ችሏል። በዚህም ምክንያት የባቡር መስመሩን 50ኛ ዓመት ማክበር የኢንጂነሪንግ ስኬቱን ከመዘከር በተጨማሪ ለአፍሪካ-ቻይና ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ያበረከተውን አስተዋጽኦ ለማድነቅም እድል ይሰጣል።

Share this article

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *