በአፍሪካ አህጉር ወደ ስራ የገባው አህጉራዊ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ወደ ስራ መግባትና የቻይና የኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ መምጣት አፍሪካን በዓለም የንግድ ስርአት ውስጥ ቁልፍ ተዋናኝ እያደረጋት የመጣ ሲሆን ለዚህ እንደአንዱ ማሳያው ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና በአለማቀፍ ገበያ ያለው ተደራሽነት የአህጉሩን አቅም ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በአፍሪካ አህጉር እና ቻይና መካከል እየጠነከረ የመጣው የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር በአለምአቀፍ የንግድ ስርአት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ማርሽ ቀያሪ የሚባል ሚናን እየተጫወተ ይገኛል ።
ከዚሁ ጋር ሊነሳ የሚችለው ቻይና በአህጉረ አፍሪካ ባላት መሪ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነትና መጠነ ሰፊ ትስስር በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪና በሸቀጦች ንግድ መስፋፋት እያደገ የመጣው የአህጉሩ መነቃቃትና የማደግ ፍላጎት አፍረካን ቀጣዩ የአለም የንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከል የሚያደርግ ነው።
እንደ አውሮፖውያኑ አቆጣጠር በ2021 የጀመረው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና 1.4 ቢሊዮን ህዝብ የያዘውን አህጉር እየፈነጠቁ ያሉ የገበያ አማራጮችና ተስፋዎችን የበለጠ የሚያጠናክር ሲሆን ሶስት ትሪሊዮን ዶላር የደረሰውን የህዝቡ የመሸመት አቅም የበለጠ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል ። ይህ አህጉራዊ እምቅ የቻይናንና ሌሎች አለማቀፍ ባለሃብቶች በአንድ አገር ጋር ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በአፍሪካን የንግድና ኢንቨስትመንት ላይ እንዲገቡ የበለጠ እድልን ይፈጥራል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የቀጣናዊ ትስስርና የንግድ ፍሰት ጉዳዮቸ ከፍተኛ ባለሙያው አቶ መላኩ ገቦያ፣ ከቻይናው ሲጂቲኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና በቻይና እና አፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ላይ ሊያመጣቸው የሚችሉ እድሎችን በስፋት ያብራራሉ ።
“የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መመስረት ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን ከአህጉረ አፍሪካ ውጭ ለሚገኙ አገራት ጭምር የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ይሆናል ፤ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለንዋያቸውን ሲያፈሱ ኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል በማድረግ፤ ለ1.4 ቢሊዮን አፍሪካወያን የምርት የአቅርቦት ማእከል ያደርጋታል ። ኢትዮጵያ ደግሞ ለቻይናውያን ባለሃብቶች ቁልፍ ስታራቴጂክ ማዕከል በመሆን ቁጥር አንድ መዳረሻ መሆን ትችላለች ” ይላሉ።

የቀጣናዊ ትስስርና የንግድ ፍሰት ጉዳዮቸ ከፍተኛ ባለሙያው እንደሚሉት ቻይና ለሁሉም አፍሪካ አገራት ወደ አገሯ ለሚገቡ ምርቶች የፈቀደችው ከቀረጥና ታክስ ነፃ የገበያ እድል አጋዥና ምቹ የሚባሉ የንግድ ፖሊሲ በመሆኑ ይህ ሌላኛው ተስፋ ሰጭና አዳጊ አጋርነት መኖሩን ማሳያ ነው።
ይሁን እንጂ ለእንደዚህ አይነት ኢንሸቲቮች መሳካትና ግባቸውን ሊመቱ የሚችሉት በመንግስታት እና የግሉ ዘርፍ ጠንካራ ቅንጅትና ትበብር አማካኝ ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ለንግድና ቢዝነስ ማህበረሰቡ እነዚህን ማዕቀፎችና እድሎች የማስተጋባትና አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ግድ ይለዋል የሚሉት አቶ መላኩ ኢትዮጵያዊያን ከቻይና ባለሃብቶች ጋር የሚያደርጉት ትብብር ሁለቱንም በሚጠቅም መልኩ እየሄደ መሆኑ መረጋገጥ አለበት ይላሉ።
በተጨማሪም አፍሪካ የንግድ ሰንሰለቱን አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ማድረግ አለበት ያሉት ባለሙያው ጥሬ እቃን ባለበት ደረጃ ወደ ውጭ ገበያ መላክ በቂ ባለመሆኑ ምርቶች ላይ እሴት የመጨመርና የሚመረቱ ምርቶችን ደግሞ የራሳቸው የሆነ መለያ ብራንድ እንዲኖራቸው በማድረግ የንግዱና ኢንቨስትመንት ማህበረሰቡ በትክክለኛው መንገድ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።
በቻይና እና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን ተጨባጭና የሚታይ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ የሚላከውን ቡና መመልከት በቂ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል ። ከዚህ ቀደም ትንሽ ይባሉ የነበሩትን ጨምሮ የቻይና የቡና ገበያዎች በከፍተኛ ሁኔታ እያደጉ የሚገኝ ሲሆን ባለፍት ጥቂት አመታት ከኢትዮጵያ ይላክ የነበረው የቡና ምርት በአስር አጥፍ አድጎ በአውሮፖውያኑ አቆጣጠር 2024 ላይ 12ሽህ ቶን ደርሷል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ቡና አምራችና ላኪዎች ማህበር ፐሬዚዳንት አቶ ግዛት ወርቁ በቅርቡ ከቻይናው ሲጂቲኤን ጋር በነበረቸው ቃለመጠይቅ ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና ገበያ የሚላከው የቡና መጠን በፍጥነት እያደገ መሆኑን ያብራራሉ ። አክለው ሲያብራሩ “በሰባት አመታት ውስጥ እኛ ወደቻይና የላክነው ቡና ከ1270 ቶን ወደ 36 ሽህ ቶን አድርጓል ፣ ይህ የሚያሳየው ለኢትዮጵያ ቡና ምን ያክል የገበያ እድል መኖሩን ነው” ይላሉ።
በኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ቀዳሚ ከሆኑ ላኪዎች መካከል የትራኮን ትሬዲንግ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ሰይድ ኡመር በበኩላቸው “የቻይና ሸማቾች የኢትዮጵያን ቡና ከፍተኛ የተባለውን ዋጋ ከፍለው ይገዛሉ፣ ምርታችን ከታክስና ቀረጥ ነፃ እንዲገባ ከመደረጉ ባለፈ በቻይና ለኢትዮጵያ ቡና ባለው አመለካከት እየጨመረ በመምጣቱ ነጋዴው ምርቱን ወደ ቻይና ለመላክ ያለው ፍላጎት ከሚታሰበው በላይ እየጨመረ ነው “ በማለት ይገልፁታል ።
ለዚህ እያደገ ለመጣ ፍላጎትና የንግድ ስርአት መሳለጥ ደግሞ የመሰረተ ልማት መስፋፋትና ዘመናዊ ማቀነባበሪያ ማሽነሪዎች ወሳኝነታቸው የማያሻማ ይሆናል። አቶ ሰይድ ድርጅታቸው ዘመናዊ ወቅቱ የሚፈልገውን ቴክኖሎጂና መሰረት ልማት የተሟላላቸው ማዕከላትና የደንበኞችንና የተጠቃሚውን ፍላጎትና ጀረጃ በሚያሟላ መንገድ ምርትን የሚዘጋጁና ይህንኑን ተግባር በየቀኑ የሚፈፅሙ 350 ባለሙያዎች እንዳሏቸው ይገልፃሉ።
ይህ የእለት ተዕለት ተግባር ለኢትዮጵያ የቡና ገበያ ምቹ ምህዳር ከፈጠረው የቻይና የንግድ ፖሊሲና ስርአት ጋር በማጣጣም አሁን ካለው በበለጠ ለመላክና በቻይና እና ኢትዮጵያዊ እንዲሁም በቻይና እና አፍሪካን መካከል ያለውን የንግድ ትብብር የማሳደግ እድሉ ከፍተኛ ይሆናል ።

በአጠቃላይ ሲታይ ቻይና ከአፍሪካ አህጉር ጋር ያላት ትብብር ከቡና ገበያ በላይ ነው። በተለይም በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረጉ ትብብሮች በአህጉሩ የተቀናጀ የአቅርቦት ሰንሰለትን የሚፈጥር ነው።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናንና የቻይናን አስቻይ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎችን በመጠቀም አህጉሩ በሚያደርገው የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምርትን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ምድር ያሉ ኢንዱስትሪዎችን መነቃቃትን የሚፈጥርና የበለጠ እንዲያመርቱ የሚደርግ ነው።
የቀጣናዊ ትስስርና የንግድ ፍሰት ጉዳዮቸ ከፍተኛ ባለሙያው አቶ መላኩ እንደገለፁት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና የንግድ ሰራአት ብቻ ሳይሆን የኢንቨስትመንት ዋነኛ መሳሪያ መሆን አለበት። በዚህ ረገድ ቻይናውያን ባለሃብቶች በአፍሪካ ምድር የሚያፈሱት መዋዕለ ነዋይ ራሳቸውን ኩባንያዎቹን ከመጥቀም ባለፈ የአፍሪካዊያን የማደግና የመለወጥ ህልም እውን የሚያደርግ ነው። ይህ በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን ግንኙነትና ትብብር በስርአቱ መምራትና ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ማስኬድ ከተቻለ በቻይና እና አፍሪካ መካከል የአዲሱ ዘመን ሌላኛው የትብብር ታሪክ ይሆናል።












