በዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ(ዲ.አር.ሲ.) ምስራቃዊ ክፍል እየተካሄደ ያለው ግጭት የሩዋንዳና የኮንጎ መሪዎች በአሜሪካ ዋሽንግተን የሰላም ስምምነቱ በፈረሙ በሰአታት ውስጥ ተባብሶ መቀጠሉን ሮይተርስ ዘግቧል። ስለ ስምምነቱ ለማንበብ
በፕሬዝዳንት ትራምፕ ታሪካዊ ነው የተባለው ይህ ስምምነት በማዕንድን በበለጸገው ቀጠና ለአስርት አመታት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም ያለመ ነበር።
የኮንጎው ፕሬዝዳንት ፍሌክሲ ትሽስኬዲና የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በዋሽንግተን ተገኝተው ባለፈው ሀምሌ ወር በአሜሪካ አደራዳሪነት ለተፈረመው የሰላም ስምምነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳየትቻውና የአሜሪካ ኩባንያዎች በማዕድን ማውጣት እንዲሰማሩ መንገድ መክፈታቸው ተገልጾ ነበር።
ነገርግን መሬት ላይ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው፤ ተፋላሚ ኃይሎቹ አንዳቸው ሌላኛቸውን በመክሰስ ላይ ናቸው።

በዚህ አመት መጀመሪያ በምስራቃዊ ኮንጎ መብረቃዊ ጥቃት በመክፈት ሁለት ትልልቅ ከተሞችን የተቆጣጠረው እና በዋሽንግተኑ ስምምነት ያልታቀፈው የኤም-23 አማጺ ለኮንጎ መንግስት ታማኝ የሆኑ ኃይሎች መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተዋል ብሏል።
የኮንጎ ጦር ቃል አቀባይ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውንና የሩዋንዳ ጦር እየደበደበ መሆኑን ገልጿል።
ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ የአሜሪካ ዲፕሎማሲ በምስራቃዊ ኮንጎ ያለውን ውጥረት ቢያረግበውም ወሳኙን ጉዳይ አለመፍታቱንና ሩዋንዳም ሆነች ኮንጎ በሐምሌው ስምምነት የገቡትን ቃል አልተገበሩም።
በዛሬው እለት በኦንላይን የሚዘዋወሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ንብረቶቻቸውን እና ከብቶቻቸውን ይዘው በምስራቃዊ ኮንጎዋ ሳውዝ ኪቩ ግዛት ሉቪንጊ ከተማ አቅራቢያ በእግራቸው ሲሰደዱ አሳይቷል።
የምስራቃዊ ኮንጎ ግጭት መነሻ
በምስራቃዊ ኮንጎ ያለው ግጭት የተነሳው እ.ኤ.አ. በ1994 በሩዋንዳ የሁቱ ጎሳ ታጣቂዎች አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የቱትሲ ጎሳ አባላትን፣ ለዘብተኛ ሁቱዎችንና ትዋ የተባሉ ነባር ህዝቦችን ከገደሉ በኋላ ነበር።
በቱትሲ የሚመራው ኃይል ባደረገው ማጥቃት በቀልን የፈሩ 2 ሚሊዮን ገደማ ሁቱዎች ድንበር አቋርጠው ኮንጎ ለመግባት ተገደዱ። ሩዋንዳ እነዚህን የተሰደዱ ሁቱዎች በዘር ማጥፋት የተሳተፉ መሆናቸውንና የኮንጎ ጦር ክፍል ከለላ እየሰጣቸው እንደሆነ ትከሳለች። በሁቱዎች የተደራጀው ሚሊሻ ለዋሩንዳ ቱትሲ ህዝብ አደጋ መደቀኑን ትገልጻለች።
ኮንጎ በአንጻሩ ይህን ክስ በማስተባበል የሩዋንዳ ጦር ከግዟታ ለቆ የማይወጣ ከሆነ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንደሚያስቸግር ሲገልጽ ቆይቷል።












