የ“Trump Gold Card” ቪዛ፣ ሀብታም የውጭ ሀገር ዜጎች ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ በመፈጸም የተፋጠነ የአሜሪካ ነዋሪነት ፍቃድ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። በፕሮግራሙ መሰረት፣ ግለሰቦች የቪዛ ሂደቱን የማስጀመሪያ 15ሺህ ዶላር በመክፈል እና ማጣሪያው ሲጠናቀቅ፥ ለአሜሪካ መንግስት 1 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይኖርባቸዋል። ኩባንያዎችም ለአንድ ሰራተኛ 2 ሚሊዮን ዶላር በማዋጣት የውጭ ሰራተኞችን ስፖንሰር ማድረግ ይችላሉ።
ፕሮግራሙ አሁን ያሉትን በልዩ ችሎታ፣ ብሄራዊ ጥቅም እና በግል ብቃት ላይ ተመስርቶ የሚሰጡ የኢቢ-1 እና ኢቢ-2 የስደተኛ ቪዛ ፕሮግራሞችን ይተካል የሚል ስጋት አለ።

ከዚህ በተጨማሪ፥ ጎብኚዎች የማህበራዊ ሚዲያ መረጃቸውን እንዲያስመረምሩ የሚያስገድድ ህግ ሊወጣ መሆኑን በአሜሪካ Federal Register ገጽ ላይ የወጣው ማስታወቂያ ይገልጻል። እቅዱ ህግ ሆኖ ከጸደቀ ያለ ቪዛ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ጎብኚዎች የአምስት አመታት የማህበራዊ ሚዲያ ታሪካቸውን እና ሌሎች የግል መረጃዎቻቸውን አንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል። ህጉ ተፈጻሚ የሚደረገው ቪዛ እንዲኖራቸው ሳይጠየቁ ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ፍቃድ ላገኙ፥ 42 የአውሮፓ እና እስያ አገራት ተጓዦች ይሆናል። የእነዚህ አገራት ተጓዦች ወደ ኢምባሲዎች መጓዝ ሳይጠበቅባቸው በቀላሉ ማንነታቸውን የሚያጣራ የኤሌክትሮኒክ ማረጋገጫ ስርዓት ውስጥ ማለፍ ብቻ የሚጠበቅባቸው የነበረ ቢሆንም፥ አዲሱ እርምጃ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርግባቸዋል።
ህጉ ከጸደቀ ጎብኚዎች ባለፉት አምስት ዓመታት እና ከዚያም በላይ የተገለገሉባቸውን የማህበራዊ ሚዲያ ዩዘርኔም፣ የኢሜል አድራሻዎቻቸውን እና የስልክ ቁጥራቸውን፣ የቅርብ የቤተሰብ አባላትን ስም፣ አድራሻ፣ ስልክ ቁጥሮች እና የልደት ቀኖችን እና ሌሎች መረጃዎችን እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ።
በሰኔ ወር የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ለኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ባስተላለፈው መመሪያ የአሜሪካ ዜጎች፣ ባህል፣ መንግስት እና ተቋሞች ላይ “የጥላቻ አመለካከት ያላቸው” የተማሪ ቪዛ አመልካቾች ላይ ማጣራት እንዲያዲያደርጉ ጠይቆ ነበር።
በእነዚህ መመሪያዎች መሰረት አመልካቾች ፕሮፋይላቸውን ለህዝብ እንዲታይ ይፋ እንዲያደርጉ የሚጠየቁ ሲሆን፥ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ አለመሆን በማመልከቻው ሂደት ጥርጣሬን ሊያስነሳባቸው የሚችል እንደሚሆን ያመላከተ ነበር።
አዲሱ እቅድ የትራምፕ አስተዳደር ባለፉት 11 ወራት ውስጥ በሁሉም የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ እየተገበረ ያለው ከፍተኛ የምርመራ ዘመቻ አካል ሲሆን ይህም እያንዳንዱን በህጋዊም ሆነ ህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የሚደረግ ጉዞ በሙሉ የሚመለከት ይሆናል። እርምጃው በአሜሪካ ቱሪዝም ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችል እንደሆነ በአንድ የዋይትሃውስ ዝግጅት ላይ የተጠየቁት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፥ “ደህንነትን እንፈልጋለን፣ ትክክለኛ ያእሆኑ ሰዎች ወደ አገራችን እንዲገቡ መፍቀድ የለብንም” በማለት መልሰዋል።












