ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ቻይና በ 4 ቢሊዮን ዶላር የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ ለመዘርጋት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ቻይና ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ወደ ጁቡቲ በተዘረጋው የባቡር መስመር ፕሮጀክት ላይ ግዙፍ ተቋራጮቿን በግንባታ ላይ በማሳተፍ እንዲሁም ፋይናንስ በማድረግ ለቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ወሳኝ አስተዋጽኦ አበርክታለች።

ይህ የጋዝ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ልክ እንደ አዲስ አበባ-ጁቡቲ የባቡር መስመር ሁሉ እቃ ለማጓጓዝ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማምጣት ታልሞ የተቀረጸ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ ቻይና በአፍሪካ ውስጥ እያካሄደች ያለው የኢኮኖሚ ትብብር ከሁለትዮሽ ወደ ብዙ ሀገራት አሳታፊነት ለማሳደግ ቁርጠኛ እየሆነች መምጣቷን ያሳያል።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖራትም፣ እነዚህን ሀብቶች ለአለምአቀፍ ገበያ ለማቅረብ ወደበ የላትም። በአንጻሩ ይህ ነው የሚባል የተፈጥሮ ሀብት የሌላት ጅቡቲ፣ በአለም እጅግ ወሳኝ በሆነው የባህር መስመር ላይ ትገኛለች። ቻይና ደግሞ በፋይናንስ፣ የምህንድስና ባለሙያዎችን በማቅረብና አስተማማኝ የጋዝ (LNG) ገበያ በመሆን አስፈለጊ ነች። ስለሆነም ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ የሶስቱ ሀገራት ትብብር የየራሱ አሳማኝ ምክንያት ያለው መሆኑን ያመለክታል።
እንዳቸው ሌላኛቸው የሌላቸውን ጥንካሬ በማዋጣት፤ የተናጠል ጥንካሬን ወደ ጋር አቅም ቀይረውታል።
700 ኪሎሜትር ገደማ የሚሆነው ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ፣ የተፈጥሮ ጋዝን ከኢትዮጵያ ወደ ጁበቲው ዳመርጆግ የፈሳሽ ጋዝ ማጠራቀሚያና የኤክስፖርት ጣቢያ ያስተላልፋል።

በእርግጥ ይህ ፕሮጀክት፣ ጋዝን ወደ ውጭ ከመላክ የዘለለ ፋይዳ ያለው ነው። በባቡር፣ በመንገድና በኃይል ማሰራጫ በተፈጠረው የኢትዮጵያና ጅቡቲ ትስስር ላይ ተጨማሪ ድራብ ይሆናል። እነዚህ ፕሮጀክቶች በቀጣናው ሰዎች፣ እቃዎችና ኢንቨስትመንት በነጻነት የሚዘዋወሩበት የኢኮኖሚ ትስስር ይፈጥራሉ።
ይህ ዓይነቱ ትስስር አስፈላጊ የሚሆነው መሠረተ ልማቶች እንደ ተናጠል ፕሮጀክቶች ሳይሆን እንደ አንድ የተቀናጀ ሥርዓት ሲሰሩ የበለጠ ውጤታማ ስለሚሆኑ ነው። ባቡር የመጓጓዣ ወጪን ይቀንሳል፤ የተረጋጋ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ኢንዱስትሪን ያበረታታል፤ ዘመናዊ ወደቦች ንግድን ያፋጥናሉ፤ የጋዝ ቧንቧዎችም የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ገበያ ያደርሳሉ። እነዚህ መሠረተ ልማቶች እርስ በርሳቸው ሲደጋገፉ፣ ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪ እና ለሥራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ ማለት ነው።
ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ላይ እየታየ ያለውን አዲስ ለውጥ ያንጸባርቃል። ይህ ትብብር ከተለመደው “የሰጭ-ተቀባይ” ግንኙነት ይልቅ በጋራ ጥቅሞች ላይ ወደተመሰረተ ትብብር መሸጋገሩን አመላካች ነው። ኢትዮጵያ ወደ ዓለም የኃይል ገበያ የምትወጣበትን መንገድ የምታገኝ ሲሆን ጅቡቲ ደግሞ ክልላዊ የሎጂስቲክስና የኃይል ማዕከልነቷን ታጠናክራለች።ቻይናም የረጅም ጊዜ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ ይረዳታል። እንዲህ አይነቱ ትብብር ሶስቱንም ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ መካከላቸው ያለውን ትብብር የበለጠ በማጠናከር ሚናው ከፍተኛ ነው።

ጎረቤት ሀገራት የየራሳቸውን ጥንካሬ በማጣመር የጋራ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ የሚያሳይ ተግባራዊ ምሳሌ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በሀገራት መካከል ያለው ርቀት ከዚህ በኋላ የትብብር እንቅፋት ሊሆን እንደማይችልም የሚያሳይ ነው።
ፕሮጀክቱ በታቀደው ጊዜ ከተጠናቀቀ፣ ከአንድ ትልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት በላይ ትርጉም ይኖረዋል። ሌሎች ተመሳሳይ ፕሮጀከቶች እዲተለሙና እንዲሰሩ ያበረታታል። በተጨማሪም በጋራ ጥቅም፣ በትስስር እና በተግባራዊ ትብብር ላይ የተመሰረተ ክልላዊ ውህደት (economic integration ) የአፍሪካን ቀንድ የኢኮኖሚ ገጽታ እንደሚቀይር ማሳያ ይሆናል።
ከሁለም በላይ ከዚህ ትብብር መረዳት የሚቻለው የአፍሪካ ሀገራት የየራሳቸውን አቅም ማዋጣትና መተባባር ከቻሉ እንዲህ አይነት ግዙፍ የልማት ስራዎች እውን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው። ለዚህ ትብብር ደግሞ ቻይና ፋይናንስና በቴክኖሎጂ በማቅረብ ተጨማሪ አቅም ሆና ብቅ ማለቷም ግልጽ ሆኗል።











