አፍሪካ የራሷን ሰላምና ጸጥታ በራሷ አቅም መምራት ዋነኛ ፍላጎቷ ቢሆንም፣ ከቻይና ጋር የሚደረግን ትብብር ግን በበጎ ነው የምትቀበለው። በቤጂንግ የተካሄደው 4ኛው የቻይና–አፍሪካ የሰላምና የጸጥታ ፎረም ይህንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በዚህ ፎረም ላይ ሁለቱ ወገኖች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እያደርጉ ያለዉን ትብብር በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችም ለመድገም ቁርጠኝነታቸዉን አሳይተዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት በቻይና ቋሚ ተወካይ አምባሳደር አልሃጂ ሳርጆህ ባህ በፎረሙ ላይ ባቀረቡት ንግግር አፍሪካ ሰላም ለማስከበር የቻይና ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነ ታምናለች፡፡“የአፍሪካ ጸጥታ የአፍሪካ ኃላፊነት ነው” ያሉት አምባሳደሩ ይህ ግን አፍሪካ ከዓለም ራሷን ማግለል አለባት ማለት አይደለም ብለዋል። አምባሳደሩ እንዳሉት “የራስን ባለቤትነት በመተማመን መጠቀም እና አፍሪካዊ ሉዓላዊነትን ከሚያከብሩ አጋሮች ጋር መተባበር” አስፈላጊ ነዉ። አምባሳደሩ ቻይና የአፍሪካ ወሳኝ አጋር የሆነችዉ፣ የአፍሪካን ሉአላዊነት ስለምታከብርና ጸጥታዋን በራሷ እንድትመራ ድጋፍ ስለምታደርግ ነዉ ብለዋል፡፡
የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ዶንግ ጁንም በፎረሙ ላይ ተመሳሳይ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ሲጂቲአን አንደዘገበዉ ዶንግ የቻይና እና አፍሪካ የጸጥታ ትብብር ለሁለቱም ወገኖች ልማት እና ለዓለም አቀፍ መረጋጋት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ሚኒስትሩ የቻይና ጦር ኃይልም ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ስትራቴጂያዊ ቅንጅትን፣ የባሕር ጸጥታን እና የመከላከያ አቅም ግንባታን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የተቀሰቀሱ የእርስበርስ ግጭቶች ባልቆሙበትና በመካከለኛዉ ምስራቅ ያለዉ ጦርነት የአለም ቁልፍ የንግድ መተላለፊያዎችን ደህንነት አደጋ ላይ በጣለበት ወቅት፣ የቻይና እና አፍሪካ ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ የቻይና ድጋፍ ለአፍርካ ራስበቅነት ጉልህ አስተዋጻኦ ይኖረዋል፡፡
አፍሪካ የምትፈልገው የውጭ ድጋፍ ብቻ አይደለም፤ የምትፈልገው የራሷን አቅም መፍጠር ነው። ትብብሩ ተቋማትን የሚያጠናክር፣ የአፍሪካን የራስ መተማመን የሚያሳድግ እና በቀጣይ የአህጉሪቱን ችግሮች በራሷ እንድትፈታ የሚያስችል እንዲሆን ትፈልጋለች። ቻይና ደግሞ ለዚህ አይነት ትብብር ምቹ ነች፡፡
አምባሳደር ባህ ለአፍሪካ ሀገራት “የማንኛውም አጋርነት ዋነኛ ዓላማ መተካት ሳይሆን ማብቃት ነው።” ይህ ምናልባት የንግግሩ ዋና መልዕክት ነው። አጋር ማለት የአፍሪካን ሚና የሚወስድ ሳይሆን አፍሪካ የራሷን ሚና በተሻለ አቅም እንድትወጣ የሚያግዝ ነው።ይህ ጉዳይ በተለይ አፍሪካን ካጋጠሟት የጸጥታ ችግሮች አንጻር ወሳኝ ነው። ሽብርተኝነት፣ ጽንፈኝነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል፣ ሕገወጥ ዝውውር፣ የባሕር ጸጥታ እና የሳይበር ስጋት ጠንካራ የጋራ ምላሽ ይፈልጋሉ። በዚህ ረገድ የቻይና ልምድና ሀብት ለአፍሪካ ጠቃሚ የሆነ ድጋፍ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ዘላቂ ጸጥታ በወታደራዊ አቅም ብቻ አይገነባም። ሥራ ዕድል፣ ትምህርት፣ መሠረተ ልማት፣ ንግድ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድልም የጸጥታ ጉዳዮች ናቸው። አምባሳደር ባህ እንዳሉት፣ “ልማት ራሱ በጸጥታ ላይ የሚደረግ ክፍተኛ ኢንቨስትመንት ነው።”
ቻይና ለአፍሪካ የሰላምና የጸጥታ ጥረቶች የምታደርገው ድጋፍ፣ ከዱዋላ የአፍሪካ ኮንቲኔንታል ሎጂስቲክስ ቤዝ ድጋፍ ጀምሮ እስከ የአቅም ግንባታና የመከላከያ ትብብር ድረስ፣ ይህንን አጋርነት ከቃል ወደ ተግባር ለማሸጋገር ያለውን አቅም ያሳያል።
የቻይና እና አፍሪካ የጸጥታ አጋርነት ዋናው ጥያቄ ማን ለአፍሪካ ይሠራል የሚለው ሳይሆን፣ አፍሪካ ከአጋሮቿ ጋር በመተባበር የራሷን አቅም እንዴት ትገነባለች የሚለው ነው። የአምባሳደር ባህ መልዕክትም በዚህ ላይ ያተኮረ ነው፤ አፍሪካ “ብቻዋን ለመቆም” ሳይሆን “በመተማመንና በክብር” ከምታምናቸው አጋሮች ጋር መሥራት ትፈልጋለች። ይህ የአጋርነት ሀሳብ ወደተግባር ከተቀየረ፣ ትብብሩ የጸጥታ ትብብር ብቻ ሳይሆን የተቋማት ጥንካሬ፣ የልማት ዕድልና ዘላቂ ሰላም መሠረት ሊሆን ይችላል።
የአለም ሁለተኛ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ የሆነችዉ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ላላት ግንኙነት ከፍተኛ ትኩረት ትሰጣለች፡፡በዚህ አመት ሚያዚያ ወር ይፋ ያደረገችዉና 53 የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ ያደረገዉ የቀረጥ ነጻ እድል ትልቅ የሚባል ማሳያ ነዉ፡፡










