ከኢትዮጵያ በተለያዩ ሁኔታዎች ወጥተው የነበሩ 17 ጥንታዊ የብራና መንፈሳዊ መጻሕፍት ወደሀገር መመለሳቸዉን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።
ከተመለሱት ቅርሶች መካከል ታምረ ማርያም፣ አርባዕቱ ወንጌል፣ ስንክሳር፣ መዝሙረ ዳዊት፣ ድርሳነ ሚካኤል፣ አርጋኖና ወዳሴ እና የዮሐንስ ወንጌል ይገኙበታል። አንዳንዶቹ ከ17ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፉ ታሪካዊ የእጅ ጽሑፎች ናቸው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ቅርሶቹን ከተረከበ በኋላ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ጽ/ቤት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት፣ ለኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም፣ ለማኅበረ ቅዱሳን እና ለመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ ጨምሮ ለተለያዩ ተቋማት አስረክቧል።
በርክክቡ ውቅት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው እነዚህ ውድ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱበት ታላቅ ቀን መሆኑን ገልጸው፣ ሌሎች ከሀገር የወጡ ቅርሶችን የማስመለስ ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል ብለዋል። ቅርሶቹ ለትውልድ እንዲተላለፉ፣ በባለሙያዎች እንዲጠኑ እና ለትምህርትና ምርምር እንዲውሉ በአግባቡ እንዲጠበቁም አሳሰበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አርቲስት አብራር አብዶ ለ20 ዓመታት በአደራ ጠብቆ ያቆየውን የራሱን ምስል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በስጦታ አበርክቷል። ዋና ዳይሬክተሩም የአርቲስቱ ተግባር ጥበብን የማክበርና አደራን የመጠበቅ ትልቅ ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል።የተመለሱት ቅርሶች በተገቢው ሁኔታ መጠበቃቸውና ለጥናትና ምርምር መዋላቸው የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና መንፈሳዊ ትውፊት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ጠቃሚ መሆኑ ተገልጿል።













