በአሁኑ ወቅት በቻይና ሱፐርማርኬቶች ስንዘዋወር ከተለመዱት የሀገር ውስጥ ምርቶች የተለዩ ምርቶች ወደ ገበያ እየገቡ ናቸው። የኬንያ አቮካዶ፣ የቤኒን አናናስ፣የደቡብ አፍሪካ ታንጊ ቲንደሪን በመላው ቻይና በሱፐርማርኬቶች ላይ ተደርድረው ይታያሉ። የእነዚህ ትኩስና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የአፍሪካ የግብር ምርቶች ወደ ዋና የቻይና ገበያዎች መግባት፣ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተው የቻይና-አፍሪካ የንግድ ትብብር እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ሁነኛ ምሳሌ ነው።
ቻይና ተግባራዊ ባደረገችው የዜሮ-ታሪፍ ፖሊሲ፣ ባልተጠበቀው የገበያ አቅርቦትና ከፍተኛ ፍላጎት የተበረታቱት፣ ግዙፎቹ የቻይና ሱፐርማኬቶች የአፍሪካ የግብርና በማሳደግ በደቡባዊ ንፍቀክበብ ለሚገኙ ሀገራት (Global South Countries) ጠንካራና የረጅም ጊዜ እድሎችን እያመጡ ናቸው።
ቻይና በዚህ አመት ሚያዝያ ወር መጨረሻ ከ 53 የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ መጠን ለማሳደግ የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ ይፋ ማድረጓ የሚታወስ ነው። በዜሮ ታሪፉ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ምርቶችን ወደ ሰፊው የቻይና ገበያ እየላኩ ነው። በዚህ ምክንያት ፖሊሲው ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ መጠኑ ከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
የቻይና አጠቃላይ የጉምሩክ አስተዳደር መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በግንቦትና ሐምሌ ቻይና ከአፍሪካ ያስገባቸው ከአመታዊ አማካኙ በ23.5 በመቶ ብልጫ አለው። የአቮካዶ(130 በመቶ)፣ የአፕልና(89.6 በመቶ) የብርቱካን(28.9 በመቶ) ኢምፖርት(ግዥ) ጨምሯል።

ገበያ ማስፋፋት
በዜሮ ታሪፍ መርሃግብር የመጀመሪያውን የአፕል ምርት ጭነት ወደ ቻይና ሸንዘን ባይ ፖርት በማስለፍ እድሉ ከተመቻቸላቸው 53 ሀገራት ውስጥ ተጠቃሚ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ነበረች። ከእዚያ ወዲህ ግን የኬንያ አቮካዶ፣የደቡብ አፍሪካ ወይን፣ የዚምባቡዌ ቡሉቤሪዝና ሌሎች ጥራት ያላቸው የአፍሪካ ምርቶች በቻይና ሱፐርማኬት መደርደሪያዎች ለሽያጭ ቀርበዋል።
በቅርቡ አመታት ውስጥ በተለይ ቻይና የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ወዲህ ቻይናና አፍሪካ በግብርና ዘርፍ የሚያደርጉት ትብብር እየጨመረ መጥቷል። በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተራራማ ቦታዎች ላይ በአቮካዶ ምርት ላይ እየታየ ያለው ለውጥ የዚህ ማሳያ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የቻይና ኢንተርፕራይዞች ተሳትፎ የአፍሪካ የግብርና ኢንዱስትሪ እንዲቀየርና እንዲሻሻል አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በዜሮ ታሪፍ እርምጃው ወደ ቻይና የሚልኩ ኩባንያዎች ወጭያቸውን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነሳቸው፣ ተጨማሪ በጀት ለስልጠናና ለአርሶአደሮች የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋልም ተብሏል። ቻይና ታሪፍ ከመቀነስ በተጨማሪ፣ “ግሪን ቻናልስ”ና ሌሎች መሳሪዎችን በመጠቀም ለአፍሪካ ኤክስፖርት የገበያ መዳረሻን አስፍታለች።
ከሚያዝያ መጨረሻ ጀምሮ ቻይና ለአፍሪካ የደረቅ ቃሪያ፣ የቡና ፍሬ፣ የካሽው ለውዝ እና ሌሎች ምርቶች አንድ ወጥ የኳራንቲን ማስፈቀጃ ሥርዓት መተግበር ጀምራለች። ይህም ለእያንዳንዱ ምርት በተናጠል የሚደረገውን የሁለትዮሽ ድርድር አስቀርቷል።በተመራጭ የታሪፍ አያያዝ ምክንያት ዚምባብዌ በሐምሌ ወር የመጀመሪያ የብሉቤሪ ምርት ጭነቷን ወደ ቻይና ልካለች። ይህ ጭነት ለዚምባብዌ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ትልቅ ስኬት ሲሆን፣ በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ የሸማቾች ገበያዎች ወደ አንዱ መግቢያ በር ከፍቷል።
የዜምትሬድ (ZimTrade) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አለን ማጁሩ በሰኔ ወር ባሳተሙት የጋዜጣ አምድ ላይ፣ ዜሮ ታሪፍ ለዚምባብዌ ላኪዎች በቅርብ ዓመታት ከተፈጠሩት በጣም ጉልህ የንግድ ዕድሎች አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።
“ወደ ቻይና የሚደረገው የገበያ መዳረሻ የምርት መጠንን ለማሳደግ፣ የቀዝቃዛ ሰንሰለት መሠረተ ልማትን ለማጠናከር፣ የማሸጊያ ጥራትን ለማሻሻል፣ የማረጋገጫ አቅምን ለማሳደግ እና በእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት እድል ይፈጥራል” ብለዋል ማጁሩ።

የዘመናዊነት ግብ
ዓለምአቀፉ ገበያ እየጨመሩ ባሉ እንቅፋቶች እየተፈተነ ባለበት በዚህ ወቅት ቻይና ገበያዋን ማስፋቷና ክፍት ማድረጓ ለአፍሪካ የኢኮኖሚያዊ እድገት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ታዛቢዎች እየተገነዘቡ ነው።ኬንያዊው ኢኮኖሚስት ጄምስ ሺክዋቲ እንደሚሉት፣ የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲው የቻይናና የአፍሪካን የጋራ ዘመናዊነት ግብን ወደ ተግባራዊ እርምጃ የሚቀይር ነው።
ይፋዊ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ቻይና ወደ አፍሪካ የላከቻቸው የኤሌክትሮሜካኒካል ምርቶች እኤአ በ2026 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 534.11 ቢሊዮን ዩዋን (ወደ 79 ቢሊዮን ዶላር) ደርሷል፤ ይህም ከዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር 28.8 በመቶ ጭማሪ ነው።
ወደ አፍሪካ ከሚላኩት የቻይና ምርቶች ውስጥ ወደ 75 በመቶው የካፒታልና የመካከለኛ ምርት ግብዓቶች ሲሆኑ፣ እነዚህም በዋናነት የአፍሪካን ኢንዱስትሪ ልማትና የግብርና ዘመናዊነት የሚደግፉ የምርት ግብዓቶች ናቸው።
በቻይና ፔኪንግ ዩኒቨርሲቲ የኒው ስትራክቸራል ኢኮኖሚክስ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዩ ጂያ፣ የዜሮ ታሪፍ አያያዙ አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ የአጭር ጊዜ የታሪፍ ቅናሽ ሳይሆን የቻይናና አፍሪካ የኢኮኖሚና የንግድ ትብብር አዲስ ደረጃ መድረሱን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

“ለአፍሪካ ንግዶችም ሆነ ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች፣ ተገማችነት በራሱ ለልማት ጠቃሚ ሀብት ነው” ብለዋል ዩ።
የናይጄሪያ የቻይና ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ቻርልስ ኦኑናይጁ በበኩላቸው፣ “ቻይና የምታቀርበው ከእርዳታ በጣም የሚልቅ ነው። አፍሪካ በምርት፣ በንግድና በኢንዱስትሪ እድገት የራሷን ለውጥ እንድታሳካ ወሳኝ ዕድሎችን ይፈጥራል” ብለዋል።
ኦኑናይጁ አክለውም አብዛኛው የአፍሪካ ህዝብ ወጣት መሆኑ ኢንዱስትሪያዊ ልማትን ለማሳካት ጠንካራ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።












