የያንግ ላይቭስ (Young Lives) የኢትዮጵያ ዳይክተር የሆነው እንግሊዛዊው የታሪክ ተመራማሪ አሉላ ፓንክረስት፣ “አንጸባራቂው የቴዎድሮስ መጽሐፍ ቅዱስ” በአረብ ኢምሬትስ፣ ዱባይ በነገው እለት በጨረታ ሊሸጥ መሆኑን ሊንክድኢን በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያ ገጹ አስፍሯል።
አሉላ ፓንክረስት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ከአምስት አስርት አመታት በላይ የታሪክ ምርምር ያደረጉት የታዋቂው እንግሊዛዊ የታሪክና የስነማህበረሰብ(Sociology) ተመራማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት ልጁ ነው። አሉላ የሚለው ስም የተሰጠው ጣሊያኖች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ በዱር በገል ፍልሚያ ካደሩጉት አርበኞች ውስጥ ስመጥር የሆኑትን አርበኛ ራስ አሉላ አባነጋን ለማስታወስ ነው።
በኢትዮጵያ ጥናቶች ላይ ትኩረት ያደረገው አሉላ ፓንክረት፣ ልክ አንደ አባቱ ሁሉ የኢትዮጵያን ታሪክ በቅርበት ይከታተላል።
ጨረታው ኢንሊብሪስ (INLIBRIS) በተባለ አለምአቀፍ ኩባንያ እንደሚቀርብ የገለጸው አሉላ “ይህ በእጅ የተጻፈ ቅርስ መሸጥ አለበት ወይስ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አለበት!” የሚል ጥያቄ አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ መንግስት ስለዚህ ጉዳይ በይፋ ያለው ነገር የለም።
ጨረታውን የሚያቀርበው ኢንሊብሪስ ጥንታዊ የእጅ ጹሁፎችን፣ መጽሃፍትንና ግለታሪኮችን የሚያከማች መቀመጫውን ቬና፣ ኦስትሪያ ያደረገ አለምአቀፍ ኩባንያ ነው።












