ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አለምአቀፍ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በነገሰበት በዚህ ወቅት በግብጽ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ የቻይና-አፍሪካን ሁሉንአቀፍ ትብብር ለማስፋት ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
ፕሬዚዳንት ሺ በካይሮ በግብፅ አቻቸው ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ቻይናና ግብፅ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ለመስራት ተስማምተዋል። እንደ ሲዲቲኤን ዘገባ፣ ሁለቱ ወገኖች በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ (BRI)፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የትብብር ሰነዶችን ተፈራርዋል። ፕሬዝዳንት ሺ ስምምነቶቹ ሲፈረሙ ከተመለከቱ በኋላ የካይሮ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ተመልሰዋል።
ዘገባው እንደገለጸው 70ኛ አመት የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ያከበሩት ሀገራቱ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።
ፕሬዚዳንት ሺ በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ሁለቱ ሀገራት በልማት በኩል “ተጨባጭ ትብብር ያለውን ወሰን ማስፋፋት” እንዳለባቸው ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ሲሲ በበኩላቸው ካይሮ ለአንድ-ቻይና (One-China policy) ፖሊሲ ያላትን ድጋፍ አረጋግጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቻይና በግብፅ ላይ ላደረገችው ኢንቨስትመንትም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በደቡባዊ አፍሪካ ከምትገኘው ኢስዋቲኒ በስተቀር፣ የአፍሪካ ሀገራት በአጠቃላይ ለአንድ-ቻይና ፖሊሲ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል። ይህ ፖሊሲ በቻይና የውጭ ፖሊሲ ውስጥ መሠረታዊ መርህ ነው። ይህ የዲፕሎማሲ አቀራረብ ቻይና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በተለያዩ ዘርፎች ያላትን ትብብር እንድታስፋፋ ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ ነው። በቅርቡም ከአፍሪካ ሀገራት ለሚመጡ ሸቀጦች የዜሮ ታሪፍ ዕድል መፍጠሯ የዚህ ትብብር አንዱ ምሳሌ ነው።
ግብፅ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባለው የቀይ ባህር ክልል የምትገኝ በመሆኗ፣ የስትራቴጂካዊ አጋርነቷን በማብዛት የበለጠ የፖለቲካ ተፅዕኖ ለማግኘት ትፈልጋለች። ለካይሮ፣ ከዓለም ሁለተኛዋ ባለትልቅ ኢኮኖሚ ከሆነችው ቻይና ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር፣ አሜሪካን ጨምሮ ከሌሎች ታላላቅ ኃይሎች ጋር ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ በምትደራደርበት ወቅት የድርድር አቅሟን ሊያሳድግ ይችላል።
እ.ኤ.አ. በ2024 ግብፅ ቻይና መሥራች አባል ከሆነችበት (ብሪክስ) BRICS ቡድን ጋር ተቀላቀለች። ይህ ቡድን እያደጉ ያሉ ኢኮኖሚዎች በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የምዕራባውያንን ተፅዕኖ ለመቀነስ ወይም አማራጭ መድረክ ለመፍጠር የሚጠቀሙበት መድረክ እየሆነ ነው።
እንደ ኤፒ ዘገባ ቻይና በግብፅ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት አድርጋለች። ኢንቨስትመንቱ ከካይሮ ምሥራቅ የሚገኘውን የንግድ ማዕከል እና በናይል ዴልታ የሚገኙትን የኢንዱስትሪ አካባቢዎች የሚያገለግል የኤሌክትሪክ ባቡር መስመርን ያካትታል። ኤፒ የመንግሥት አኃዞችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። ይህ አሀዝ በአሜሪካ እና ግብጽ መካከል ካለው የ 15.7 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ልውውጥ ብልጫ ያለው ነው። ግብፅ በክልሉ የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ወሳኝ አጋር ስትሆን፣ ሁለቱ ሀገራት በመሪዎቻቸው ደረጃም ቅርብ ግንኙነት አላቸው።
በፕሬዚዳንት ሺ አመራር ሥር፣ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትስስር በተከታታይ ለማጠናከር እየሰራች ነው። ይህም በአፍሪካ መሪዎች በኩል ተመሳሳይ ምላሽ አግኝቷል፤ ብዙዎቹም እያደጉ ያሉ ኢንዱስትሪዎቻቸውንና የመሠረተ ልማት እድገታቸውን ለመደገፍ ቴክኖሎጂ፣ ኢንቨስትመንትና የቴክኒክ እውቀት ከቻይና ይፈልጋሉ።
በመሆኑም የቻይናና የግብፅ ግንኙነት በአፍሪካ የሚታየውን ሰፊ ትብብር አዝማሚያ ያንጸባርቃል። የአፍሪካ መንግሥታትም የዓለም አቀፍ አጋርነታቸውን በማብዛት፣ ከዓለም ታላላቅ ኃይሎች ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ፣ መሠረተ ልማትና የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት የበለጠ እየጣሩ ናቸው።












