አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ (ኤአይ) ዓለምን በፍጥነት እየቀየራት ነው። ሀገራት እውቅ ተመራማሪዎቻቸውንና ግዙፍ ፋይናንስ በመመደብ የዘርፉን ፉክክር በቀዳሚነት ለመምራት ያለእረፍት እየሰሩ ናቸው።
ነገርግን ፉክክሩ አዳዲስና የላቁ ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግና በመፍጠር ላይ ብቻ የታጠረ አይደለም። የዲጂታል ሉአላዊነትን ማስጠበቅ መቻል ጊዜው የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። መረጃን ለመቆጣጠር፣ የቴክኖሎጂ ህጎችን ለማውጣትና በአዳዲስ ፈጣራዎች ላይ የራስን ባህል ለማንጸባረቅ የዲጂታል ሉአላዊነትን ማስጠበቅ ወሳኝ ነው። ይህ ጽንሰሀሳብ ነው የዲጂታል ሉአላዊነት የሚባለው።
ኢትዮጵያም “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂዋን በምታስፈጽምበት ወቅት በቀዳሚነት ልትመለከተው የሚገባ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ በ2030 የዲጂታል መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት፣ የመንግስት አገልግሎቶችን ለማዘመንና የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት አስፈላጊ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው። ይሁን እንጂ የሚቀጥለው ምዕራፍ ኤአን መጠቀም ብቻ ሳይሆን እሱን የመቅረጽ አቅም መፍጠር ሊሆን ይገባል። የዲጂታል ኢንቨስትመንት የኢትዮጵያን ቋንቋዎች የሚረዱ፣ ለሀገሪቱ ፍላጎቶች መፍትሔ የሚሰጡ እና የኢትዮጵያን እውነታ የሚያንጸባርቁ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር መዋል አለበት።
በዚህ ረገድ የቻይና ተሞክሮ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣል። በዘርፍ ቀዳሚ ከሆኑትና የበርካታ ግዙፍ የኤአይ ኩባያዎች መገኛ የሆነችው ቻይና እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት የምታስተምረው የኤአይ አስተዳደርና ቁጥጥር ተሞክሮ አስፈላጊነት የሚካድ አይደለም። ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፉ ትብብር ለማድረግ ከቻይና መንግስት ጋር የትብብር ማጽቀፍ ማድረጓ ይታወሳል።
እአአ 2026 በሻንጋይ የተካሄደው አለምአቀፍ የኤአይ ጉባኤ (World Artificial Intelligence Conference) ቻይና ለዲጅታል ሉአላዊነት ትኩረት መስጠቷንና ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራትን ለመደገፍ ፍላጎቷን ገልጻለች።
በጉባኤው ላይ የተናገሩ ባለሙያዎች አፍሪካ በሌሎች የተፈጠሩ የኤአይ ቴክኖሎጂዎችን የምትጠቀም ገበያ ብቻ መሆን እንደማይገባት አጽንኦት ሰጥተዋል። በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) መረጃ መሠረት፣ ከኢንተርኔት ይዘት ውስጥ ከአንድ በመቶ ያነሰው ብቻ በአፍሪካ ተወላጅ ቋንቋዎች እንደሚገኝና ከአፍሪካ የሚመነጨው መረጃ አነስተኛ ክፍል ብቻ በአህጉሪቱ ውስጥ እንደሚቀመጥ ያመላክታል። ይህ አኃዝ የሚያመለክተው የቴክኖሎጂ ክፍተት መኖሩን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቋንቋዎች፣ እውቀቶችና መረጃዎች በኤአይ ስርዓቶች ውስጥ ካልተካተቱ ከመጪው የቴክኖሎጂ አብዮት ውጭ የመቅረት አደጋ እንዳለ ነው።

ኢትዮጵያና ቻይና በኤአይ አስተዳደር ዘርፉ አብሮ ለመስራት የትብብር ውይይቶች አካሂደዋል።እአአ ጥር 2026 የቻይና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ ውይይት ካካሄዱ በኋላ ባወጡት መግለጫ “በኢኮሜርስ፣ በዲጅታል ኢኮኖሚና በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ” ዘርፎች ትብብር ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸው ነበር። ይህ ትብብር ቻይና የኤአይ ልማዷን ለማካፈል ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ እነዚህን እድሎች ለመጠቀም ዝግጁ መሆን ይጠበቅባታል።
ባለፉት ዓመታት ቻይና የዲጂታል መሠረተ ልማትን፣ የመረጃ ማዕከላትን፣ የኤአይ ምርምርን፣ የባለሙያ ሥልጠናንና ክፍት ምንጭ (Open Source) የኤአይ ሞዴሎችን በማበረታታት ጠንካራ የኤአይ ሥነ-ምህዳር ገንብታለች። እነዚህ የኤአይ ቴክኖሎጂዎች ለታዳጊ ሀገራት በዝቅተኛ ወጪ ተደራሽ ተደርገዋል። ይህ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቴክኖሎጂ ጀማሪ ድርጅቶች (Startups) እና የመንግስት ተቋማት እነዚህን ሞዴሎች በመጠቀም ለአማርኛና ለሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተስማሙ መፍትሔዎችን ማበልጸግ ይችላሉ። በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በፋይናንስና በመንግስት አገልግሎቶች ዘርፍ የሚገነቡ የኤአይ መተግበሪያዎች በኢትዮጵያ መረጃና እውቀት ላይ ሲመሰረቱ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ።
የመረጃ ማዕከላት ግንባታም ሌላ ወሳኝ ትምህርት ነው። በሀገር ውስጥ የመረጃ ማዕከላትን መገንባት የቴክኖሎጂ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሉዓላዊነትን የሚያጠናክር እርምጃ ነው። መረጃን በሀገር ውስጥ ማቆየት ደህንነትን ያጠናክራል፤ ፈጠራን ያበረታታል።ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያን እውነታ የሚያንጸባርቁና ቁጥጥር የሚደረግባቸው የኤአይ ስርዓቶችን ለመፍጠር ይረዳል።
ይህ ለማድረግ የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው። ቻይና ለታዳጊ ሀገራት 5,000 የኤአይ ሥልጠና ዕድሎችን ለመስጠት ያቀረበችው ቃል ኪዳን ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል። ተመራማሪዎች፣ መሐንዲሶች፣ የፖሊሲ ባለሙያዎችና ወጣት ፈጣሪዎች እነዚህን ዕድሎች በመጠቀም እውቀታቸውን ሀገራቸውን በሚጠቅም መልኩ ለማዋል ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በተመሳሳይ ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክ ተቋማት የኤአይ ትምህርትን በማጠናከር የራሷን የባለሙያ አቅም መገንባት አለባቸው።
ኢትዮጵያ ኤአይን በስፋት እየተጠቀመች በምትሄድበት ጊዜ ጠንካራ የኤአይ አስተዳደር (AI Governance) ሥርዓት መገንባትም ያስፈልጋል። የመረጃ ጥበቃ፣ የሥነ-ምግባር መመሪያዎች፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎች የሕዝብን እምነት ያጠናክራሉ።
ዲጂታል ሉዓላዊነት ማለት ከዓለም መነጠል ማለት አይደለም። ይልቁንም ከአጋሮች ጋር በመተባበር የራስን አቅም መገንባት ነው። የቻይና ተሞክሮ በመሠረተ ልማት፣ በሰው ኃይልና በፈጠራ ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ብሔራዊ አቅምን እንደሚያጠናክር ያሳያል። ኢትዮጵያም እነዚህን ልምዶች ከራሷ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ራዕይ ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ ፈጠራ፣ አስተዳደርና አመራር ማሳደግ ይኖርባታል። በኤአይ ዘመን እውነተኛ ልማት የሚመጣው ቴክኖሎጂን ከሚጠቀሙ ሀገራት ሳይሆን ቴክኖሎጂን በሚፈጥሩ፣ በሚመሩና በራሳቸው ሁኔታ የሚያስተዳድሩ ሀገራት ይሆናሉ።











