የኢትዮጵያና ቻይና መንግስታት፣ ቻይንኛ ቋንቋን (ማንደሪንን) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ስርአተ ትምህር ውስጥ ለማካተት ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።ይህ ስምምነት ለሁለቱም ሀገራት ከተመለደው የባህል ልውውጥና ከስርአተ ትምህርት ፖሊሲ ለውጥ ያለፈ ትርጉም ያለው ነው።
ውሳኔው ቻይንኛ ቋንቋ ሁለቱ ሀገራት ለሚያከናውኗቸው ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ወሳኝ መሳሪያ እየሆነ መምጣቱን በግልጽ የሚያመላክት ነው። ከዚህ በፊት በአብዛኛው የቻይንኛ ቋንቋ መማር ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ከባህል ዲፕሎማሲ ጋር የተያያዘ ነበር። አሁን ላይ ይህ ጭብጥ ተቀይሯል።
ለኢትዮጵያ የቻይንኛ ቋንቋን ማስተማር፣ በክህሎት፣ በስራ እድል እንዲሁም በተወዳዳሪነት ላይ የሚደረግ እንቨስትመንት ሆኗል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የቻይንኛ ቋንቋ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። እአአ እስከ 2025 መጨረሻ ድረስ ሁለት የኮንፊሽየስ ኢንስቲትዩቶችና አንድ ሉባን ዎርክሾፕ ከ60,000 በላይ የቻይንኛ ቋንቋ ተማሪዎችን አሰልጥነዋል።
የኢትዮጵያና ቻይና ትምህርት ሚኒስትሮች ቋንቋውን በስርአት ትምህርት ውስጥ ለማካተት ከስምምነት የደረሱት ሰኔ 10 ቀን 2026 ነበር። ይህን ስምምነት የፈረሙት የኢትዮጵያን ትምህርት ሚኒስቴርን በመወከል የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ክንደያ ገብረሂወት፣ የቻይናን ትምህርት ሚኒስቴር በመወከል ደግሞ በአዲስአበባ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ ናቸው። ሚኒስትር ዲኤታው ስምምነቱ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የቻይንኛ ቋንቋ መርሃግብሮችን እንዲከፍቱ እንደሚያስችል እንደሆነ በወቅቱ ገልጸዋል። አምባሳደር ቼን ሀይ በበኩላቸው ስምምነቱ በኢትዮጵያ በቅርብ አመታት ውስጥ እየተስፋፋ ለመጣው ለዚህ ቋንቋ ጥናት ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉ ነበር ያወደሱት። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ሁለቱ ሀገራት ቋንቋውን ለማስፋፋትና የኢኮኖሚ መሳሪያ ለማድረግ ያላቸው ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን ነው።

ቻይና በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት፣ በመማሪያ መጽሐፍት ዝግጅት፣ በመምህራን ሥልጠናና ደረጃውን የጠበቀ የማስተማሪያ ሥርዓት በመመሥረት ድጋፍ ታደርጋለች። ይህም የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት ከተናጠል ፕሮጀክቶች ይልቅ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የትምህርት ዕቅድ አካል እንዲሆን ያስችላል።
ቋንቋው በብሔራዊ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በተቋማዊ መልኩ መካተቱ፣ ቻይና ከኢትዮጵያ ትልልቅ የንግድና የኢንቨስትመንት አጋሮች አንዷ ያንጸባርቃል። የቻይና ኩባንያዎችም በማምረት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና በኃይል ዘርፎች ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው። የኢኮኖሚ ግንኙነቱ እየጠናከረ በመምጣቱ፣ በቋንቋና በባህል መካከል በብቃት መግባባት የሚችሉ ባለሙያዎች ፍላጎትም እየጨመረ ነው። በዚህ ምክንያት ቻይንኛ መማር የቻይናን ባህል ለመረዳት ብቻ የሚደረግ ጥረት ሳይሆን፣ የሥራ ዕድልን ለማሻሻል የሚያግዝ ክህሎት መሆኑን ነው። በዚህ ምክንያት “ቻይንኛ ከመማር” ወደ “ቻይንኛን መጠቀም” ሽግግር እየተደረገ ነው።
ቋንቋው ኢትዮጵያና ቻይና በቅርበት በሚተባበሩባቸው ዘርፎች ውስጥ ሥራ ለማግኘትና ሙያዊ አቅምን ለማሳደግ የሚያግዝ ሙያዊ ክህሎት እየሆነ ነው። በመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚሰሩ መሐንዲሶች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሰሩ ሥራ አስኪያጆች፣ ንግድን የሚያመቻቹ የጉምሩክ ባለሙያዎች፣ ከቻይና አቅራቢዎች ጋር መሥራት የሚፈልጉ ሥራ ፈጣሪዎችና እየጨመረ ላለው የቻይና ጎብኚዎች የሚያገለግሉ የቱሪዝም ባለሙያዎች ሁሉ ከቻይንኛ ቋንቋ ክህሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ። በቀጥታ መግባባት ወጪን ይቀንሳል፣ አለመግባባትን ያስወግዳል፣ የንግድ ሥራንም የበለጠ ቀልጣፋ ያደርጋል። ቋንቋ ልክ እንደ መንገድ ባቡር፣ ዲጂታል ትስስር ሁሉ ለኢኮኖሚ ትብብር ማስቻያ መሠረተ ልማት ሆኗል ያለት ይቻላል።
መስተጋብሩን በሁለቱም በኩል ለማድረግ በማሰብ ቻይናም የአማርኛ ቋንቋን በቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ (Beijing Foreign Studies University) በመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም እየሰጠች ነው። በሁለቱም ወገን ያሉት ጥረቶች ሀገራቱን ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የበለጠ ያጠናክራል።

በቻይና-አፍሪካ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አመት የተደረሰው ስምምነቱ፣ የረጅም ጊዜ ግብ ተቀምጦለታል። ቋንቋውን በመጠቀም የተሻለ ሥራ ማግኘት፣ ኢንቨስትመንትን ማመቻቸት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን መደገፍና የንግድ ግንኙነቶችን ማጠናከር የሚችሉ የኢትዮጵያ ተመራቂዎች ማፍራት ነው።
በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ውስጥ ብዙ ቋንቋዎችን የመጠቀም ክህሎት ተወዳዳሪነትን ይጨምራል።
ቻይንኛን በብሔራዊ የትምህርት ሥርዓቷ ውስጥ በማካተት፣ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት ለሚኖራት የሰው ኃይል ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት እያደረገች ነው። በተመሳሳይም ከዋና ዓለም አቀፍ አጋሮቿ አንዷ ከሆነችው ቻይና ጋር ካላት ግንኙነት የበለጠ ጥቅም ለማግኘት እየተዘጋጀች ነው።ስለዚህ ይህ ስምምነት ተራ የቋንቋ ትምህርት ተነሳሽነት ተደርጎ ብቻ ሊታይ አይገባም። ይልቁንም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት ከ“ቻይንኛን መማር” ወደ “ቻይንኛን በተግባር መጠቀም” የሚሸጋገርበትን አዲስ ምዕራፍ የሚያመለክት እንዲሁም የሀገሪቱ ሰፊ የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ አስፈላጊ አካል ተደርጎ ሊታይ የሚገባ ነው።
ቻይና በዚህ አመት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ53 የአፍሪካ የቀረጥ ነጻ (Zero Tariff) እድል ይፋ ማድረጓና በኢትዮጵያ በቻይና መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን መጨመር የቻይንኛ ቋንቋ መማርን አስፈላጊነት የበለጠ ምክንያታዊ የሚያደርጉ ናቸው።











