Loading...

የሱዳን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የመንገደኞች አውሮፕላን ለመጀመሪያ ጊዜ ካርቱም አረፈ

በሱዳን የእርስበርስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የመንገደኞች አውሮፕላን ለመጀመሪያ ጊዜ ካርቱም አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አርፏል።

በሀገሪቱ በ2023 የተመጀረው ጦርነት የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ አድርጓቸው ነበር።

በርካታ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት የሱዳን ኤየርዎይስ የሆነችው አውሮፕላን ከፖርት ሱዳን ተነስታ ነው ካርቱም ያረፈችው። ፖርት ሱዳን የካርቱም አብዛኛው ክፍል በፈጥኖ ጀራሽ ኃይሎች ከተያዘ በኋላ በጦሩ ለሚመራው መንግስት ጊዜያዊ ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች።

ነገርግን ባለፈው ወር የሱዳን ጦር ካርቱምን መልሶ መቆጣጠሩንና የመንግስት መቀመጫውን ከፖርት ሱዳን ወደ ካርቱም በይፋ ማዛወሩን ማስታወቁ ይታወሳል። የበረራው መጀመርም ጦሩ በካርቱም ላይ ያለው ቁጥጥር እየጠነከረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ተብሏል።

የሀገሪቱ ዜና አገልግሎት ሱና እንደዘገበው ይህ እርምጃ የሀገሪቱ ሁኔታ ቀስበቀስ ወደ አንጻራዊ ማገገምና መረጋጋት እየተመለሰ መሆኑን የሚያሳይ ትልቅ መሰረት ነው። ባለፈው ጥቅምት 2025 የሱዳን ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን በረራ ለመጀመር እቅድ እንዳለው አሳውቆ የነበረ ቢሆንም አየር ማረፊያ በተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት ደርሶበታል። የሱዳን ጦር በወቅቱ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተላኩ በርካታ ድሮኖችን ማክሸፉን አስታውቆ ነበር።

የካርቱም አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ስራ ማቆም በሀገሪቱ ያለውን ጉዞ በከፍተኛ ደረጃ አስተጓጉሎት ቆይቷል።

በሁለት ጀነራሎች መካከል የተጀመረው የእርስበርስ ጦርነት ሀገሪቱ በአለም ቀዳሚው የሰብአዊ ቀውስ ያለባት እንድትሆን አድርጓታል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው