የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ መሀመድ (በቅጽል ስማቸው ፋርማጆ) በስልጣን ዘመናቸው ላከናወኑት ተግባር በምስጋና መልክ በዜጎች የተገነባላቸው አዲስ መኖሪያ ቤት በይፋ ተመረቀ።
እንደ TRT Afrika ዘገባ ከሆነ ይህን ቤት ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብ የተሰበሰበው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር (Diaspora) በሚኖሩ ሶማሊያውያን በጎ ፈቃደኛ ደጋፊዎች አማካኝነት ነው።

የ”እናመሰግናለን ፕሬዝዳንት” ዘመቻ
ይህ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ በሰኔ 2022 “Thank You, Mr. President” በሚል መጠሪያ የተጀመረ ሲሆን በአጠቃላይ ወደ 300,000 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከህዝቡ ተሰብስቧል። የግንባታው ወጪ 295,000 ዶላር ገደማ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ቤቱ የተገነባው በታሪካዊቷ የባህር ዳርቻ ከተማ መርካ (Merca) ውስጥ በሚገኘው የሴልጃሌ (Ceeljaalle) አካባቢ ነው።
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በስልጣን ዘመናቸው (2017-2022) የአገሪቱን የውጭ ዕዳ በመሰረዝ፣ የመከላከያ ሠራዊቱን በማጠናከር እና የመንግስት ሀብትን በአግባቡ በማስተዳደር ረገድ የነበራቸው ሚና ደጋፊዎቻቸው ለቤቱ ግንባታ በገንዘብ እንዲሳተፉ አነሳስቷቸዋል።
የካቲት 6 ቀን 2026 በይፋ የተመረቀውን ይህን ቤት አስመልክቶ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዲህ ብለዋል፦
“ለዚህ ዘመቻ አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ የሶማሊያ ዜጎች፣ ሲቪሎች እና የጸጥታ ኃይሎች በሙሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ይህ ተግባር መንግስታዊ አመራር የህዝብ መሆኑን እና ህዝቡ ጥቅሙን የሚያስከብር መሪ ሲያገኝ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን የሚያሳይ ትልቅ መልዕክት ነው”

በሶማሊያ የቀድሞ መሪዎች እንደሌሎች ሀገራት ከፍተኛ የጡረታ አበል ወይም የመኖሪያ ቤት ጥቅማጥቅም ስለሌላቸው ይህ የዜጎች ተነሳሽነት በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ያልተለመደ እና አዲስ ምዕራፍ እንደሆነ ተገልጿል። ፋርማጆ ከዚህ ቀደም በሞቃዲሾ ውስጥ በኪራይ ቤት ይኖሩ እንደነበር ይታወሳል።
ይህ ተግባር ምንም እንኳን በሶማሊያ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች ዘንድ ትችቶችን ቢያስተናግድም ለብዙዎች ግን በመሪ እና በህዝብ መካከል ያለውን ጥብቅ ትስስር የሚያሳይ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።












