Loading...

“በኢሊት ፎርስ” በዓል ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምን አሉ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ሰላም ለማስጠበቅ የሚችል ቴክኖሎጂ የታጠቀ የልዩ ዘመቻ ኃይል ወይም አሊት ፎርስ መገንባቱን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ’65ኛው የልዩ ዘመቻ ዕዝ’ በዓል በዛሬው እለት በሀዋሳ ከተማ ሲከበር ባሰሙት ንግግር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከሶማሊ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ በባህር የሚያጋጥሙ ሽብሮችን ወንድም ህዝቦችን ደግፈን ሽብርን ለማስቀረትና ልማትና ብልጽግናን በቀጣናችን ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው በቂ የሆነ ኢሊት ፎርስ… ምሽግ ሚያፈርስ፣ ውጊያን የሚያሳጥር ተገንብቷል።”

ለኢሊት ፎርስ አባላት ያላቸውን ከፍተኛ አድናቆት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውጊያን እንዳይከሰት የማስቀረት ወይም ከተከሰተ በአጭር ጊዜ ለመቋጨት የሚችል ተቋም መገንባቱን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው የኢትዮጵያ መከላከያ የኢትዮጵያን ነጻነትና አፍሪካን ሰላም ዛሬም እንደትናንቱ ያስከብራል ብለዋል።
“ኢትዮጵያ አልተደፈረችም፤ አትደፈርም። በክብርና በነጻነት ለልጆቻችን የምናሸጋግራት ብቸኛው የአፍሪካ ፈርጥ ሆና ትቀጥላለች። የኛ ዝግጅት በድፍን አፍሪካ ሰላም ለማረጋገጥ፣ በድፍን አፍሪካ ብልጽግና ለማረጋገጥ በቀጣናችን ላሉ ሀገራት አለኝታና መከታ ጋሻ ለመሆን ነው።”

በዓሉን በሺዎች የሚቆጠሩ ሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች የታደሙበት ሲሆን ወታደራዊ ትርኢቶች ተይተውበታል፤ መፈክሮችም ተስተጋብተዋል። “ተወደደለም ተጠላም፣ ተዘግቶብን አንቀርም” የሚለው በህብረት ትርኢት የተነበበው መፈክር የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት በግልጽ ያሳየ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከ110 በላይ ሚሊዮን ህዝብ ላላት ኢትዮጵያዊ ቀይባህር የህልውና ጉዳይ መሆኑን በይፋ ከገለጹ በኋላ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ተጋሪ ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ቅራኔ ውስጥ ገብታለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርበው የመንግስታቸውን የግማሽ አመት እቅድ አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት ኢትዮጵያ አሁንም ተደራድራ ወደብ ለማግኘት እንደምትጥር በድጋሚ ተናግረዋል።

እንደ ኢትዮጵያ አየርመንገድና ህዳሴው ግድብ ከመሳሰሉ ግዙፍ ተቋማት ሸር ከመያዝ እስከ መሬት ለውጥ ድረስ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር በር መውጫ ለሚሰጣት ሀገር ያቀረበቻቸው  መደራደሪያዎች ናቸው። ነገርግን የቀይ ባህር ጠረፍን ያየዙ ሀገራት እስካሁን የመደራደር ፍላት አላሳዩም። በተለይ ኢትዮጵያ በታሪክ የእሷ እንደሆነ በምትገልጸው አሰብ ወደብ ጉዳይ ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ መግባቷ ይታወሳል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው