የኢራን አብዮታዊ ዘብ(ጦር) ባለፈው አርብ ሳኡዲ አረቢያ ውስጥ በንጉስ ሱልጣን የአየር ኃይል ሰፈር ላይ በፈጸመው ጥቃት US E-3 AWACS የተባለ የስለላ አውሮፕላን ማውደሙን አስታውቋል።
ከሳኡዲ ዋና ከተማ ሪያድ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የጦር ሰፈር በሳኡዲ አየር ኃይል የሚተዳደር ቢሆንም በአሜሪካ ኃይሎች በተደጋጋሚ ይዘወተራል።
ጥቃት መፈጸሙን ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጡት የኢራን ማዕከላዊ ወታደራዊ ቢሮ ቃል አቀባይ ኢብራሂም ዞልፋጋሪ ነበሩ። ከእዚያ በኋላ በፋርስ ዜና አገልግሎት የወጡ ተከታታይ መግለጫዎች ስለጥቃቱ ዝርዝር መረጃዎችን ይዘው ወጥተዋል። እንደመግለጫዎቹ ከሆነ ጥቃቱ ድሮኖችንና ባለስቲክ ሚሳይሎችን በማዝነብ የተፈጸመ ሲሆን የአውሮፕላኑ የማስጠንቀቂያና የመቆጣጠሪያ ስርአት “ሙሉ በሙሉ ውድመት” እንዲደርስበት አድርጓል።
ፋርስ እንደዘገበው ክስተቱ ሚሳይልና ድሮን በመጠቀም የሚፈጸሙ ጥቃቶች የመከላከያ ስርአቶችን ጥሰው ማለፉ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው። የአሜሪካና የአረብ ባለስልጣናትም ጥቃቱ መፈጸሙንና E-3 ሴንትሪ ጉዳት ከደረሰባቸው አውሮፕላኖች አንዷ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች የተለቀቁ ምስሎች E-3 ሴንትሪ ወደ ሁለት መከፈሏንና በርካታ ነዳጅ የሚሞሉ አውሮፕላኖች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ያሳያሉ። ግምታዊ ዋጋው 700 ሚሊዮን ዶላር የሆነው ይህ አውሮፕላን በ250 ኪሎሜትር ሬዲየስ ውስጥ የሚቃጡ ጥቃቶችን፣ ድሮኖችን፣ ሚሳይሎችንና ጄቶችን ለመለየት ራዳር የተገጠመለት ነው። በጦርነት ወቅት ወቅታዊ መረጃ ለወገን ኃይል በማቅረብም ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ተንታኞች ይህ አውሮፕላን ወቅታዊ መረጃዎችን በማቅረብ ወሳኝ ሚና እንደነበረውና ለመተካት ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ። የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ በክስተቱ ዙሪያ ይፋዊ ማብራሪያ ባይሰጥም 12 ወታደሮች መቁሰላቸውን አረጋግጧል።
ኢራን ቀደም ሲል በዚሁ የጦር ሰፈር ላይ በፈጸማቸው የአየር ጥቃት በአምስት የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖችን ላይ ጉዳት ማድረሷን የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዋልስትሪት ጆርናል ዘግቦ ነበር። ኢራን በጦርነቱ የመጀመሪያ ወር በበርካታ የራዳር ስርአቶች ላይ ጉዳት አድርሳለች ወይም አውድማለች።
እስራኤልና አሜሪካ በቅንጅት በኢራን ላይ የከፈቱት ጥቃት የቀጠለ ሲሆን ኢራንም ወደ እስራኤልና የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ባሉባቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ላይ የሚሳይልና ድሮን ጥቃት በማዝነብ የአጸፋ ምላሽ እየሰጠች ነው።













