ግብጽ በአረብ ባህረሰላጤ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን አለምአቀፍ የነዳጅ ዋጋ ንረት ለመቋቋም ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል በሚጠቀሙ የመኖሪያ ቤትና የንግድ ተጠቃሚ ደንበኞች ላይ ጭማሪ ማድረጓን አስታውቃለች።
የግብጽ የኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ይህ እርምጃ ለነዳጅ ግዥ የሚወጣው ወጭ በሀገሪቱ በጀት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት አካል ነው።
ዝቅተኛ መጠን ያለው ኃይል የሚጠቀሙ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ጭማሪ አይደረግባቸውም ብሏል ሚኒስቴሩ። በወር እስከ 2000 ኪሎ ዋት በሰአት የሚጠቀሙ የሚኖያ ቤት ተጠቃሚዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ የማይደረግ ሲሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል በሚጠቀሙ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ላይ የ 16 በመቶ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል። የንግድ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ደግሞ በአማካኝ በ20 በመቶ ከፍ ብሏል።
የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞስጠፋ ማድቦልይ የኢራኑ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ግብጽ ለኃይል ግዥ የምታወጣው ወጭ በእጥፍ በመጨመሩ ምክንያት፣ መንግስት የወጭ ጫናን ለመቀነስ የነዳጅ ዋጋን እንዲጨምርና የተወሰኑ የመንግስት ፕሮጀክቶችን እንዲዘገዩ ለማድረግ መገደዱን ባለፈው ወር ተናግረው ነበር። ግብጽ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው ቦታዎች ቀደም ብለው እንዲዘጉ ማድረግን ጨምሮ በርካታ እርምጃዎችን መውሰድ የጀመረችው ባለፈው ወር ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እየጨመረ ያለውን የነዳጅ ዋጋ ለመቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።











