የአሜሪካ ፌደራል ፍርድ ቤት በትናንትናው እለት ባሳለፈው ውሳኔ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ለ5000 ኢትዮጵያዊያን ተስጥቶ የነበረውን ጊዜያዊ ከለላ( ከአሜሪካ ያለመባር ጊዜያዊ መብት) ለማቋረጥ ያሳለፈውን ውሳኔ አግዶታል።
በቦስትን የአሜሪካ ዲስትሪክት ዳኛ የሆኑት ብሪያን ሙርፊ ያሳለፉት ውሳኔ የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ13 ሀገራት የመጡ ስደተኞችን ጊዜያዊ ከላላ ለማቋረጥ ጥረት በሚያደርገው የትራምፕ ጥብቅ የስደተኞች አጀንዳ ላይ ትልቅ እንቅፋት ሆኖበታል።
በአሜሪካ ህግ መሰረት ስደተኞች፣ ጊዜያዊ ከለላ የሚሰጣቸው የትውልድ ሀገራቸው የተፈጥሮ አደጋ፣ የትጥቅ ግጭት ወይም ሌሎች የተለዩ ክስተቶች ሲፈጠሩ ነው።
የካቲት 6፣2018 ዓ.ም. የትራምፕ አስተዳደር ከለላውን ለማቋረጥ የወሰነው፣ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ገምግሞ እንደሆነና በግምገማውም ኢትዮጵያዊያን ይህን መብት ለማግኘት የሚያስችሉ መስፈርቶችን እንደማያሟሉ በመግለጽ ነበር።
በባይደን አስተዳደር የተሾሙት ዳኛ ሙርፊይ ትራምፕ በ2025 ወደ ዋይትሀውስ ከተመሱ በኋላ እየወሰዷቸው ከነበሩት እርምጃዎች አንጻር በኢትዮጵያውያን ላይ የተወሰደው እርምጃ የሚጠበቅ ነበር ብለዋል። ዳኛው እንዳሉት ከሆነ ትራምፕ ውሳኔውን ያሳለፉት በሀገር (በኢትዮጵያ) ውስጥ ያለውን ሁኔታ ትርጉም ባለው መልኩ ገምግመው አይደለም ሲሉ ተችተዋቸዋል።
ዳኛው አክለውም የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያቤቱ ኢትዮጵያ ውስጥ “የትጥቅ ግጭትና የተፈጥሮ አደጋ አደገኛ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ባሉበት ሁኔታ” የኢትዮጵያዊያንን ከለላ ማንሳት፣ ኮንግረሱ በጊዜያዊ ከለላ ዙሪያ ያስቀመጣቸውን አሰራሮች መጣስ ነው ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ጊዜያዊ ከለላ “በዘላቂነት ለመኖሮ በፍጹም ቲኬት መሆን የለበትም” ይላሉ።
ሶስት ኢትዮጵያዊያንና የአፍሪካ ማህበረሰብ ቡድን በጋራ በመሆን የትራምፕ አስተዳደር የትጥቅ ግጭትን ጨምሮ ያሉ አደገኛ ሁኔታዎችን ችላ ብሎ አልፏል ሲሉ ተከራክረዋል። ከሳሾቹ የትራምፕ አስተዳደር ያቀረባቸው ምክንያቶች ትክክልኛ አይደሉም፤ ሰበቦች ናቸው ብለዋል።
ዳኛ ሙርፊይ ባለፈው ጥር ወር ለኢትዮጵያውያን የተሰጠው ከላላ በየካቲት ወር እንዲያበቃ የተላለፈውን ውሳኔ በድጋሚ ለማየት በሚል እግድ ጥለውበት ነበር።












