አይ ኤም ኤፍ (IMF) – በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ጦርነት የዓለምን ኢኮኖሚ ዕድገት እያጨለመው ነው

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ትናንት ባወጣው ሪፖርት፣ በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት የዓለምን ኢኮኖሚ ወደ ከፋ ቀውስ ሊከት እንደሚችል አስጠነቀቀ። በተለይም የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት እና በነዳጅ ማምረቻ ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት ታይቶ የማይታወቅ የኃይል አቅርቦት ቀውስ (Energy Crisis) ሊያስከትል እንደሚችል ተቋሙ ገልጿል።

ተቋሙ እ.ኤ.አ. የ2026 የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ቀደም ሲል ከነበረበት 3.4 በመቶ ወደ 3.1 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጓል። ጦርነቱ ባይከሰት ኖሮ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በታየው መነቃቃት ምክንያት ዕድገቱ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

የዋጋ ግሽበት ስጋት

የነዳጅ እና የሸቀጦች ዋጋ መጨመር የዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበትን በ2026 ወደ 4.4 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ተብሏል። ይህም በቅርብ ዓመታት የታየውን የዋጋ ግሽበት የመቀነስ ሂደት ወደ ኋላ የሚመልስ ነው

የዓለምን 20 በመቶ ነዳጅ የሚያስተላልፈው የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ለዓለም ኢኮኖሚ ትልቅ ፈተና መሆኑን የጠቀሰው አይ ኤም ኤፍ ግጭቱ የሚራዘም ከሆነ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ወደ 2 በመቶ ሊወርድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በተለይ ነዳጅ ወደ አገር የሚያስገቡ እና ታዳጊ አገራት (እንደ ኢትዮጵያ ያሉ) ከቀውሱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዱ ተጠቁሟል። የነዳጅ ዋጋ መጨመር በምግብ እና በትራንስፖርት ወጪ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተገልጿል።

በጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ምክንያት አገራት ለመከላከያ የሚያወጡት በጀት መጨመሩ ለጊዜው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ቢፈጥርም በረጅም ጊዜ ግን የመንግስታትን ዕዳ እንደሚጨምርና ለማህበራዊ አገልግሎቶች የሚውለውን በጀት እንደሚቀንስ ሪፖርቱ አሳይቷል።

የአይ ኤም ኤፍ ዋና ኢኮኖሚስት ፒየር ኦሊቪዬ ጎሪንቻስ እንደገለጹት “ዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት ታላቅ ፈተና ላይ ይገኛል። የግጭቱ መራዘም የዓለምን የኃይል እና የምግብ ዋጋ በማናር የዜጎችን የመግዛት አቅም በእጅጉ ይጎዳል። አገራት ይህንን ድንገተኛ አደጋ ለመቋቋም ፖሊሲዎቻቸውን ዳግም ሊፈትሹ ይገባል።”

ተቋሙ አገራት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ እንዲከተሉ እና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከዋጋ ንረት እንዲከላከሉ መክሯል

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው