ኢራን ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች ካልተሟሉ ከአሜሪካ ጋር ለድርድር አትቀመጥም- የኢራን አፈጉባኤ

የኢራን ፓርላማ አፈጉባኤ ሞሀመድ ባጋር ሁለት ቁልፍ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ከአሜሪካ ጋር ድርድር እንደማይጀመር ተናግረዋል።

አፈጉባኤው እንዳሉት “በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ሁለቱ እርምጃዎች እስካሁን ተግባራዊ አልሆኑም፤ እነሱም በሊባኖስ የተኩስ አቁሙን ተግባራዊ ማድረግና እንዳይንቀሳቀሱ የተደረጉ የኢራን ሀብቶችን መልቀቅ ናቸው። እነዚህ ሁለት ነገሮች ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት መሟላት አለባቸው።”

አፈ ጉባኤው ይህን ያሉት ለአንድ ሳምንት ያህል የተደረገውን የኢራንና አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በፓኪስታን አስተናጋጅነት በነገው እለት ድርድር ለማድረግ ወደ እስላማባድ ባቀኑበት ወቅት ነው።
በአሜሪካ በኩል በምክትል ፕሬዝደንት ዲ ጄ ቫንስ የሚመራ የተደራዳሪ ቡድን ወደ ስፍራው ማቅናቱ ተዘግቧል።

በፓኪስታን ምልጃ የተሳካው የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤልና አሜሪካ በኢራን ላይ ሲፈጽሙ የነበረውን መጠነሰፊ ጥቃትና የኢራንን አጸፋዊ እርምጃ ለጊዜው ጋብ እንዲል ቢያደርገውም፣ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የከፈተችው ከፍተኛ ጥቃት ስምምነቱን እየፈተነው ይገኛል።

ኢራን ተኩስ አቁም ሊባኖስን ማካተት እንደሚገባውና ያ ካልሆነ ግን ከስምምነቱ ልትወጣ እንደምትችል እያስጠነቀቀቾ ነው። በዚህ ድባብ ውስጥ ሆነው ነው አሜሪካና ኢራን በእስላማባድ ለመነጋገር ቀጠሮ የያዙት። የእስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርገው ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ስምምነቱ በአጭር የመምከን እድል ይኖረዋል የሚል ስጋትን አጭሯል።

የኢራን ጦር እስራኤልና አሜሪካ “በተደጋጋሚ ተኩስ አቁሙን በመጣሳቸው” ምክንያት “ለመኮስ አቀባብሎ” እንደሚገኝ አስጠንቅቋል።

ከጦርነቱ በኋላ ኢራን ወሳኝ የነዳጅ መተላለፊያ  የሆነውን የሆርሙዝ ሰርጥን በመዝጋት ከፍተኛ የፖለቲካ መደራደሪያ አቅም ያገኘች ሲሆን አሜሪካ ደግሞ ከኑክሌር ጉዳይ ዝቅ በማለት በጦርነቱ ሳቢያ በተፈጠሩ አዳዲስ አጀንዳዎች ላይ ለማተኮር ተገዳለች።
ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ የሚያልፉ መርከቦችን እንደምታስከፍልና ከእስራኤልና አሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦችን እንቅስቃሴ ከነአካቴውም ልታግድ እንደመትችል እየገለጸች ነው።

አሜሪካ ሰርጡን ለማስከፈት ሌሎች ሀገራት እንዲተባበሯት ስትጠይቅ፣ ሩሲያና ቻይና የወረራ ጥሪ ነው በሚል ተቃውመውታል

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው