የ240 ሚሊዮን ዶላሩ የአሜሪካ ድሮን ውድቀት እና የመካከለኛው ምስራቅ ወታደራዊ ሚዛን

መካከለኛው ምስራቅ በአሁኑ ወቅት የጦር መሣሪያዎች መሞከሪያ ብቻ ሳትሆን እጅግ ውድ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መቃብር እየሆነች ትገኛለች። የአሜሪካ ባህር ኃይል ያረጋገጠው ዜና በአቪዬሽን እና በወታደራዊው ዓለም ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል። የአሜሪካ ባህር ኃይል አይኑ ተደርጎ የሚወሰደው እና እጅግ ዘመናዊው MQ-4C Triton ድሮን በፋርስ ባህረ ሰላጤ ላይ ተከስክሷል።

የ”ባህር ላይ ንስሩ” ውድቀትና የ1 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ

ይህ አደጋ የተከሰተው አሜሪካ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ብቻ 24 የሚሆኑ MQ-9 Reaper የተባሉ ድሮኖቿን ባጣችበት ወቅት መሆኑ ኪሳራውን እጅግ የከፋ ያደርገዋል። እንደ ወታደራዊ ተንታኞች ገለጻ አሁን የወደቀው MQ-4C Triton ዋጋ ብቻውን 240 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው። ይህ ዋጋ በአሁኑ ወቅት የዓለምን ሰማይ እየተቆጣጠሩ ካሉት F-35 ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች ዋጋ በእጥፍ የሚበልጥ ነው።

የአሜሪካ ባህር ኃይል ድሮኑን ያጣው በፋርስ ባህረ ሰላጤ ላይ ለስለላ ተልዕኮ ተሰማርቶ ባለበት ወቅት መሆኑን ገልጿል። ድሮኑ ከመውደቁ በፊት በ50 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ሆኖ የድንገተኛ አደጋ መልዕክት ቢልክም ከአየር ላይ ተከስክሶ ከመውደቅ ግን አልተረፈም።

አደጋ ወይስ ጥቃት?

አሜሪካ ክስተቱን አደጋ (Mishap) ብላ ብትጠራውም በብዙዎች ዘንድ ግን ጥርጣሬ ፈጥሯል። የኢራን ወታደራዊ ምንጮች ድሮኑ በራዳር ስርአታቸው ክትትል ሲደረግበት እንደነበርና በቴክኖሎጂ እርምጃ ሳይመታ እንዳልቀረ ፍንጭ እየሰጡ ይገኛሉ።

ይህ ድሮን በ250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ማንኛውንም እንቅስቃሴ የመለየት አቅም ያለው ቢሆንም አሁን የገጠመው ውድቀት የአሜሪካን የቴክኖሎጂ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል። ሚያዝያ ወር ብቻ ለአሜሪካ ባህር ኃይል እና ለአየር ኃይሉ እጅግ አስከፊ ወር ሆኖ አልፏል። እስካሁን በደረሰው ኪሳራ ብቻ አሜሪካ ከ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸውን ድሮኖች አጥታለች።

ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አንድምታው

ይህ ተከታታይ ውድቀት የሚያሳየው ቀደም ሲል የነበረው የአሜሪካ ድሮኖች ያለ ከልካይ የመብረር አቅም አሁን ላይ ፈተና ገጥሞታል። የኢራን እና የአካባቢው ኃይሎች የሚጠቀሙባቸው የኤሌክትሮኒክስ የጦርነት ስርአቶች (Electronic Warfare) እና የሚሳይል መከላከያዎች አቅማቸው ማደጉን ያሳያል።

አንድ ድሮን በ240 ሚሊዮን ዶላር ማጣት ለአሜሪካ ግብር ከፋዮችም ሆነ ለወታደራዊ በጀቱ ከባድ ጫና ነው። በተለይ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቀጣናዎችም ወታደራዊ ዝግጅት እያደረገች ባለችበት ወቅት እንዲህ አይነት ኪሳራ ለመተካት ጊዜ የሚወስድ ነው።

MQ-4C Triton ውድቀት በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን የቴክኖሎጂ ጦርነት አዲስ ምዕራፍ ላይ አድርሶታል። አሜሪካ በቀጣይ ተመሳሳይ ኪሳራዎችን ለመከላከል ምን አይነት እርምጃ ትወስድ ይሆን? ወይስ ይህ የድሮኖች መቃብርነት ይቀጥላል? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ትኩረት ሆኖ ይቀጥላል

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው