እስራኤልና ሊባኖስ ለ10 ቀናት ተኩስ ለማቆም ተስማሙ

በአሜሪካ አደራዳሪነት ንግግር ሲያደርጉ የነበሩት እስራኤልና ሊባኖስ ለ 10 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስታውቀዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁንና የሊባኖሱን መሪ ጆሴፍ አውንን ወደ ዋሽንግተን እንደሚጋብዙና እኤአ ከ1983 ወዲህ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው ትርጉም ያለው ውይይት እንዲያካሄዱ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ሁለቱም ወገኖች ለሰላም ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል።

ተኩስ አቁሙ በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከሌሊቱ 6:00 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

በቅርቡ እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ የሄዝቦላ ታጣቂዎች ይገኙባቸዋል በምታላቸው ቦታዎች መጠነሰፊ ጥቃት ስትፈጽም ቀይታለች። ይህን ኢራንን አስቆጥቷል።

ሄዝቦላን እንደአጋር የምታየው ኢራን ከአሜሪካ ጋር የደረሰችው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት በሊባኖስ ተፈጻሚ እንዲሆን ትሻ ነበር። ኢራን እስራኤልና አሜሪካ የከፈቱባትን ጦርነት ተከትሎ የዘጋችውን የሆርሙዝ ሰርጥ ለመክፈት ካቀረበቻቸው ቁልፍ ቅድመ ሁኔታ ውስጥ አንዱ ተኩስ አቁሙን በሊባኖስ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ነበር።

የሊባኖሱ ተኩስ አቁም፣ አሜሪካና ኢራን የደረሱት ተኩስ አቁም ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲያመራ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ ተጥሎበታል

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው