Loading...

አሜሪካና ኢራን የአጭር ጊዜ ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸው ተዘገበ

Trump

አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ውስንና ጊዜያዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተቃረቡ መሆናቸውን ሮይተርስ ምንጮችንና ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።

እንደዘገባው ከሆነ የስምምነት ረቂቅ ጦርነቱን የሚያስቆም ቢሆንም አብዛኞቹን አጨቃጫቂ ጉዳዮች በይደር የሚተው ነው።

ይደረሳል የተባለው ስምምነት የረጅም ጊዜ የስላም እቅድ ከመሆን ይልቅ የአጭር ጊዜ መሆኑ በሁለቱ ሀገራት ጥልቅ ክፍፍል ውስጥ መሆናቸውንና በዚህ ወቅት የሚደረስ ማንኛውም ስምምነት መሸጋገሪያ እንደሚሆን የሚያመላክት ነው ተብሏል። በከፊልም ቢሆን የሚደረግ ስምምነት የሆርሙዝ ሰርጥ እንዲከፈት ሊያደርግ ይችላል የሚል ተስፋ በመፈጠሩ፤ የአለም የካፒታል ግብይት (stock market) በከፍተኛ መጠን እንዲጨምርና ነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ አድርጓል።

ዋሽንግተንና ቴህራን በተለይም በኢራን የኑክሌር መርሃግብር ዙሪያ ያላቸው ልዩነት ለውጥ ባለማሳየቱ ምክንያት ዘላቂ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚለው ጉጉት አልተሳካም። ከዚህ ይልቅ ግጭቱ እንዳያገረሽ በመከላከልና በሰርጡ ያለውን የመርከቦች እንቅስቃሴ በማረጋጋት ላይ ነው ትኩረት ያደረጉት።
“ዋናው ጉዳያችን ጦርነቱ በዘላቂነት እንዲቆም ማድረግ ነው፤ ሌላው ጉዳይ ወደ ቀጥተኛ ንግግሩ ሲመለሱ ጊዜ ወስድው ይመክሩበታል” ሲሉ የሁለቱን ሀገራት ድርድር የተከታተሉ ከፍተኛ የፓኪስታን ባለስልጣናት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

እንደዘገባው ከሆነ የስምምነት ሀሳቡ ሶስት ምዕራፎች ይኖሩታል። ጦርነቱን በይፋ ማቆም፣ በሆርሙዝ ሰርጥ ያለውን ቀውስ መፍታትና ሰፊ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ለ30 ቀናት የሚቆይ መስኮት መክፈት ናቸው።

ፓኪስታን እንደገለጸችው በሁለቱ ወገኖች መካከል ያሉት ልዩነቶች አሁንም እንዳሉ ቢሆንም ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል አንድ ገጽ ያለው ስምምነት ሊፈርሙ ከጫፍ ደርሷል።

ጦርነቱ ከተጀመረበት እአአ ከፌብሩዋሪ 28፣2026 ጀምሮ ድል እንደሚያስመዘግቡ ሲዝቱ የቆዩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተሰፋ ሰጭ ንግግር አድርገዋል

ትራምፕ “ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ፤ ይህ የሚቻል ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ይህ የስምምነት ሀሳብ እአአ በአፕሪል 7፣2026 በተደረሰ የተኩስ አቁም ስምምነት የቆመውን ጦርነት በይፋ የሚያስቆም ነው ተብሏል።  ኢራን አሜሪካና እስራኤል የከፈቱባትን ጦርነት ለመበቀል በወሰደችው እርምጃ እስራኤልን እንዲሁም የአሜሪካ የጦር ሰፈር ያሉባቸውን የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በማጥቃቷ ጦርነቱ ሰፊ ቀጠና እንዲሸፍን አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ ኢራን ቁልፍ የነዳጅ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ሰርጥ መዝጋቷ አለምአቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው