ኢትዮጵያና ቻይና፣ የቻይንኛ ቋንቋን(ማንደሪን) የብሔራዊ ስርአተ ትምህርት አካል ለማድረግ የሚያስችል የ5 አመት ስምምነት በትናንትናው እለት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴርን በመወከል የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ክንደያ ገብረሂወት፣ የቻይናን ትምህርት ሚኒስቴር በመወከል ደግሞ በአዲስአበባ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ ፈርመውታል።
ስምምነቱ በዋናነት በኢትዮጵያ ውስጥ የቻይንኛ ቋንቋን በማስተዋወቅ ዙሪያ እንደሚያተኩር የገለጹት ሚኒስትር ዲኤታው ክንደያ የቻይና አስተማሪዎች ቋንቋውን የሚያስተምሩባቸው በርካታ የማሳያ ፕሮጀክቶች( pilot projects) በበርካታ ትምህርት ቤቶች ይጀመራሉ ብለዋል።

ሚኒስቴር ዴኤታው እክለውም ስምምነቱ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የቻይንኛ ቋንቋ ፕሮግራም እንዲከፍቱና በቀጣይነት እንዲሰጥ እንደሚደግፍ ተናግረዋል።
አምባሳደር ቼን ሀይ ስምምነቱ በቅርብ አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፋ ለመጣው የቻይንኛ ቋንቋ ጥናት ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
እስካሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የኮንፊከስ ኢንስቲትዩት የቻይንኛ ቋንቋን ለማስተማር ጥረት ማድረጋቸውን የገለጹት አምባሳደሩ አሁን ግን ስምምነቱ የቻይንኛ ቋንቋን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስርአተ ትምህርት አካል ማድረጉ ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል።
“በአዲስ አበበና በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ቤቶች መረጣ ይደረጋል። ይህ የወጣቱ ትወልድ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ቻይንኛ ለመማር እድል እንዲያገኙ፣ ስለቻይና የበለጠ እንዲያውቁና በቻይናና ኢትዮጵያ መካከል የግንኙነት ድልድይ እንዲሆኑ በር ይከፍል” ብለዋል አምባሳደሩ።
የቻይንኛ ቋንቋ ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን ህጻናትና ተማሪዎች እንደሚሰጥ የገለጹት አምባሳደሩ ቻይናም ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ትኩረት መስጠቷንና የተወሰኑ የቻይና ዩኒቨርስቲዎችም አማርኛ ቋንቋ እያስተማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ክንደያም እንደገለጹት የቻይንኛ ቋንቋ መስፋፋት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የባህል ልውውጥና የህዘብ ለህዝብ ግንኙነት ያጠናክራል።
ኢትዮጵያ “ከቻይና ጋር ላላት የቆየ ወዳጅነትና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች” ያሉት ክንደያ የሁለቱ ሀገራት ትብብር በርካታ ዘርፎችን ያካተተ እንደሆነም ገልጸዋል።
ክንደያ “ትብብራችን በትምህርት፣ በመሰረተልማት፣ በቴክኖሎጂ፣ በንግድ፣ በቱሪዝም እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ዘርፎች እየሰፋ ነው። ትምህርት ዋና የሁለትዮሽ ትብብራችን ምሰሶ መሆኑን በአጽንኦት መናገር እንፈልጋለን። ይህ ዛሬ የፈረምነው ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የትምህርትና የባህል ትብብር የሚያጠናክር ትልቅ ምዕራፍ ነው” ብለዋል።
ቻይና መምህራን በማቅረብ፣ በስኮላርሺፕ፣ የትምህርት ቁሳቁስ በማቅረብና የአቅምግንባታ ስልጠና እድሎች በማመቻቸት ለቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት ቁርጠኝነት እንዳላት የጠቀሱት ክንደያ ኢትዮጵያ በዚህ ስምምነት በስርአተ ትምህርት ቀረጻና በመምህራን ስልጠና ተጠቃሚ ትሆናለች ብለዋል።
ክንደያ በስምምነት የተካተቱት የስኮላርሺፕ እድሎችና የመምህራን ስልጠና መርሃግብሮች፣ ኢትዮጵያ ቻይንኛ ቋንቋ የሚስተምሩ የራሷን መምህራንና የቋንቋ ባለሙያዎች እንድታፈራ የሚያስችል ነው ብለዋል።











