የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ዳሬክተር ጀኔራል አቶ ሬድዋን ሁሴን በጋራ ለአልጀዚራ በጻፉት ጽህፍ አክራሪ ያሉት የህወሓት ቡድን “በመጭዎቹ ቀናት” ውስጥ የፌደራል መንግስትን ለማጥቃት ወስኗል ብለዋል።
ባለስልጣናቱ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች በአስመራ፣ በመቀሌና በሱዳን “በድብቅ እና በጣም ድብቅ በሆነ መንገድ” ስብሰባ ማድረጋቸውንና ሌላ ዙር ጦርነት ለመክፈት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።
ባለስጣናቱ በጹህፋቸው በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል በተፈረመው የዘላቂ ሰላም ስምምነት(CoHA) ደስተኛ አልነበረም ያሉትን የኤርትራን መንግስት ህወሓትን ጨምሮ “ጽምዶ” የተባለ ቡድን በማስተባበር ከሰዋል።
“አክራሪ የሆነው የህወሓት ቡድን በኤርትራ መንግስት እየተረዳና እየተበረታታ በመጭዎቹ ቀናት ውስጥ በፌደራል መንግስት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ወስኗል” ሲሉ ጽፈዋል።
ህወሓት የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስና የራሱን “ህገወጥ” አስተዳደር በማቋቋም የፕሪቶሪያውን ስምምነት በግልጽ ጥሷል ያሉት ባለስልጣናቱ አሁን ላይ በኤርትራ ቀጥተኛ ድጋፍ ተዋጊዎችን “እየመለመለ፣ እያሰለጠነና እያስታጠቀ” እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ባለስልጣናቱ በህወሓትና በኤርትራ መንግስት ላይ ተጽዕኖ ማሳድር የሚችል ማንኛውም አካል ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ግጭት እንዳይገቡ ከፍተኛ ጫና ማሳደር እንደሚገባው በጹህፋቸው አሳስበዋል።
እነዚህ ሁለት ከፍተኛ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት በጦርነቱ ወቅት በተቃራኒው ጎራ የተሰለፉ ነበሩ። አሁን የፌደራል መንግስት ባለስልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በጦርነቱ ወቅት የህወሓት ቃል አቀባይና በድርድሩ ላይ ደግሞ በህወሓት በኩል የስምምነት የፈረሙ ሲሆን አቶ ሬድዋን ሁሴን ደግሞ በፌደራል መንግስት በኩል ዋና ተደራዳሪ ነበሩ።
ስምምነቱን ተከትሎ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሆነው ተሾመው የነበሩት አቶ ጌታቸው፣ በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ከሚመራው ቡድን ጋር ቅራኔ ውስጥ በመግባታቸው ነበር ክልሉን ቀጥሎም ፓርቲውን ለቀው ለመውጣት የወሰኑት።
ውጥረቱ ባየለበት በዚህ ወቅት የአፍሪካ ህብረትን በመወከል የፕሪቶሪያው ስምምነት ዋና አደራዳሪ የሆኑት ኦሊሰጎን ኦባሳንጆ በትናንትናው ወደ ትግራይ ክልል አቅንተው፣ ከፌደራል መንግስት ጋር ቅራኔ ውስጥ ከገባው ከእነ ዶ/ር ደብረጽዮን አስተዳደር ጋር ውይይት አድርገዋል።
ኦባሳንጆ ከዶ/ር ደብረጽዮን ጋር አሁን ላይ የተፈጠሩ ውጥረቶች ለማለዘብ የሚያሰችል “ውጤታማ” ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ህወሓትም በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ለሰላም ዝግዱ መሆኑን በመግለጽ፣ የፌደራል መንግስቱን የፕሪቶረያውን ስምምነት ተግባራዊ ባለማድረግ ሲከስ ይደመጣል።
በትግራይ ክልል የፌደራል መንግስትና ህወሓት በስምምነት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያቋቁሙ ተስማምተው ነበር። ነገርግን ህወሓት ወደ ሁለት መከፈሉን ተከትሎ በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን አሁን ላይ ከጦርነቱ በፊት የነበረውን ምክርቤት ወደ ስልጣን በመመለስ የትግራይ ህጋዊ ወኪል መሆኑን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ እውቅና እንደማይሰጥ ገልጿል።ወደ ስራ የተመለሰው ምክር ቤት ከከጦርነቱ መቀስቀስ በፊት የነበሩትን ዶ/ር ደብረጽዮን በድጋሚ በፕሬዝዳንትነት እንዲሁም ሌሎችን አባሎችን በካቢኔ አባልነት መሾሙን ማስታወቁ ይታወሳል።
በፌደራል መንግስት እውቅና ያለውና በፕሬዝዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የእነ ዶ/ር ደብረጽዮንን ቡድን አካሄድ ወደ “ግጭት የሚያመራ” ነው በማለት በጽኑ ማውገዙ ይታወሳል።








