የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ትናንት በጻፉት ደብደባ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ፊት ለፊት መገናኘትና አራት አመታት ያስቆጠረውን ጦርነት ማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ መነጋገር እንደሚፈልጉ ግለጽ አድርገዋል።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ አሜሪካን ጨምሮ ለሌሎች ሀገራት በተላከው በዚህ ይፋዊ ደብዳቤ፣ አብዛኞቹ ሩሲያውያን በዩክሬን ሚሳይሎችና ድሮኖች፣ በነዳጅ እጥረትና በኑሮ ውድነት መሰላቸታቸውንና ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አሜሪካ አሁን ትኩረቷን በኢራን ጦርነት ላይ ማድረጓን የገለጹት ዘለንስኪ በአውሮፓ ያለው ጦርነት የትኩረት ማዕከል እስከሚሆን መጠበቅ ስህተት ነው ብለዋል።
ዘለንስኪ አክለውም ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ንግግር ለማድረግ የሚያስችል ሙሉ ተኩስ አቁም መድረስ ትክክለኛው አካሄድ እንደሚሆን ተናግረዋል። ዘለንስኪ እንዳሉት አሜሪካ ተኩስ ኡቀም በሚደረስበት ወቅት በግንባር ያሉ ሁኔታዎችን የመከታተል አቅም አላት።
ንግግሩ መቼ መካሄድ እንደሚችል ሃሳብ ያቀረቡት ዘለንስኪ ቱርክ፣ ስዊትዘርላንድና በአረብ አለም ያሉ በርካታ ሀገራትን በመጥቀስ “መሪዎች ግጭቶችን እንዲፈቱ በማስተናገድ የቆየ ልምድ ያላቸው በርካታ ሀገራት አሉ” ብለዋል።
“ከዚህ ጦርነት ለመውጣት አትፍራ። አሁን ካንተ የሚጠበቀው ዋነኛው ነገር ይህ ነው” ሲሉ ጽፈዋል ዘለንስኪ።
“ዩክሬን ይህን ጦርነት በቀጥታ ውይይት ለማስቆም ዝግጁ ናት። በእኔና በእርስዎ መካከል ቀጥተኛ ስብሰባ እንዲደረግ እጠይቃለሁ። ይህን ጦርነት ለማቆም ጊዜው እንደደረሰ ካላመኑ፣ ዩክሬን ለህልውናዋ መታገሏን ትቀጥላለች” ሲሉ ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ዘለንስኪ በተጨማሪም ጦርነቱ መቀጠሉ በፑቲን የፖለቲካ አቋም ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጠቁመዋል።
“እርስዎ በደንብ የሚያውቁት አንድ የሩሲያ የታሪክ እውነታ አለ፤ ሩሲያ ከጦርነትና ከችግር ስትደክም ለውጥ ይመጣል” ብለዋል።
የሩሲያ መንግስት በበኩሉ የዘለንስኪን ደብዳቤ መቀበሉን ገልጾ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን ስለ ደብዳቤው መረጃ እንደሚቀርብላቸው አስታውቋል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪል ሲቢሃ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንደጻፉት ደብዳቤው በዲፕሎማሲያዊ መንገዶችም በይፋ እንደሚላክ ገልጸዋል።
ሲቢሃ ደብዳቤውን “ጦርነቱን ለማስቆም የቀረበ ቁምነገር ያለው ሀሳብ፣ ግልጽና ተግባራዊ እርምጃዎችን እንዲሁም የፊት ለፊት ስብሰባ ጥሪን የያዘ” ሲሉ ገልጸውታል።
“ለዚህ ሀሳብ ትርጉም ያለው ምላሽ እንጠብቃለን። ጦርነቱን ለማቆምና ሰላምን ለመምረጥ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።









