የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ በዛሬው እለት ሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ ደርሰዋል።
ይህ ጉብኝት አሜሪካ በእስያ ያላትን የተጽዕኖ ሚዛን ሊቀይር እንደሚችል የሚያመላክት ነው ተብሏል።
ሺ በፒዮንግያንግ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ፕሬዚዳንት ሺ ቀጥሎም ወደፒንግያንግ ዋና አደባባይ ነበር ያቀኑት። በቦታው የተሰበሰበው በሺህ የሚቆጠረው ህዝብ ለፕሬዚዳንቱ አክብሮቱን ገልጾላቸዋል።በአደባባዩ ዙሪያ ያሉ ሕንፃዎች የሁለቱ ሀገራት ባንዲራዎች፣ የኪም ጆንግ ኡን እና ሺ ጂንፒንግን ምስሎች እና “ወዳጅነት እና አንድነት” በሚያመለክቱ መፈክሮች ተሸፍነው ነበር።

የአቀባበሉ ድምቀት ሰሜን ኮሪያ ለሺ ጉብኝት የምትሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ያመለክታል።
መሪዎቹ በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ተንታኞች ጉብኝቱ የቻይና–ሰሜን ኮሪያ ግንኙነትን እንደሚያጠናክርና እና አሜሪካ በእስያ ውስጥ ባለት የኃይል ሚዛን ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸዋል።
በአሜሪካ ማዕቀብ ስር የምትገኘው ሰሜን ኮሪያ ከቻይና ጋር ጠንካራ የሚባል የንግድና የኢኮኖሚ ትብብር እያደረገች ነው። ሺ ወደ ሰሜን ኮሪያ ሲያቀኑ በሰባት አመታት ውስጥ ይህ የመጀመሪያቸው ነው። ሁለቱ መሪዎች ባለፈው መስከረም በቤጂንግ በተካሄደው ወታደራዊ ትርኢት ላይ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሌሎች የውጭ ሀገራት መሪዎች ጋር ተገናኝተው ነበር።
የቻይና እና ሰሜን ኮሪያ ግንኙነት “በአዲስ ታሪካዊ መነሻ” ላይ እንደሚገኝ ሽኝዋ ዘግቧል።
እንደ ኤፒ ዘገባ ከሆነ ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ ግንኙነት እና ከአሜሪካ ጋር በሚያደርጉት የተለያዩ ግጭቶች ላይ ሊወያዩ ይችላሉ። ከደቡብ ኮሪያ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ያለችው ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ጫና ተጎድታለች፤ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነትን እንደ እፎይታ ትመለከተዋለች።
ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያና አሜሪካ
ሰሜን ኮሪያ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት የአሜሪካን ጫና ለመቋቋም በሚያስችል መንገድ የመጠቀም ፍላጎት አላት።
ቻይና በኮሪያ ባህረሰላጤ ሰላም እንዲሰፍን እንደምትፈልግ ከመግለጽ ውጭ፣ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር መርሃግብር በቀጥታ ስትቃወም አልተደመጠችም።
ዋይትሀውስ ባለፈው ወር ትራምፕ እና ሺ ጂንፒንግ በቤጂንግ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ባወጣው መግለጫ መሪዎቹ የሰሜን ኮሪያን ኑክሌር ለማስወገድ በጋራ እንደሚሰሩ መግባባታቸውን አስታውቆ ነበር። ነገር ግን ቻይና በኑክሌር ጉዳይ ውይይት መደረጉን በጥቅሉ ከመግለፅ ውጭ የሰሜን ኮሪያን ኑክሌር ማስወገድ (denuclearization) ጉዳይ ውይይት ስለመደረጉ ገልጽ አላደረገችም።
የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት በተለይ ኪም ዮ ጆንግ፣ የዋይትሀውስን መግለጫ “የውሸት መረጃ” ሲሉ አጣጥለውታል።
በዚህ መካከል የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መርሃግብር በፍጥነት ቀጥሏል። ኪም ጆንግ ኡን አዲስ የኒውክሌር ንጥረ ነገር ማምረቻ ተቋም በማስጀመር የሀገራቸውን የኑክሌር ኃይል ለማጠናከር ቃል ገብተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ኪም አዲስ የባህር ኃይል መርከብ ሙከራ ተመልክተዋል፤ የኑክሌር መርከብ ኃይል ለማጠናከር ጥረት እንዲደረግም ማሳሰቢያ ስጥተዋል።
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሊ ጃይ ማይንግ ሰሜን ኮሪያ በዓመት 10–20 የኑክሌር ቦምቦች ለማምረት የሚችል ንጥረ ነገር እያመረተች እንዳለች እና አህጉር አቋራጭ የሚደርስ ሚሳይል ቴክኖሎጂ ለማሻሻል መቃረቧን ተናግረዋል።
ኪም ዮ ጆንግ የአሜሪካን የኑክሌር ትጥቅ የማስፈታት ጥሪ የማይተገበር ህልም ያሉት ሲሆን ኪም ጆንግ ኡን የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በመተው በሀገሪቱ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ማዘመን ላይ ትኩረት አድርገዋል።








