የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን(ኤአይ) ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያለውን ስትራተጂካዊ ጠቀሜታ የተረዳው የኢትዮጵያ መንግስት ኤአይን ወሳኝ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ አድርጎ እየሰራበት ነው።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት እንዲሁም በቅርቡ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ዩኒቨርስቲ የመሳሰሉ ተቋማት መመስረት፣ መንግስት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ይህ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማምረት፣ ምርምርን ለመደገፍ እንዲሁም በአካዳሚ፣ በመንግስትና በኢንዱስትሪ መካከል ትብብርን ለመፍጠር የሚያስችል ብሔራዊ የልህቀት ማዕቀል(Center of Execellence) ሆኖ እንዲያገለግል መቋቋሙ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።መንግስት በኤአይ ዘርፍ ራስን ማዘመን፣ ሁለንተናዊ አለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው የሚል እምነት ከያዘ ቆይቷል።

በኤአይ የበለጠ ተወዳዳሪ ለመሆን በራስ ከሚደረጉ ጥረቶች በተጨማሪ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ካካበቱ ሀገራት ልምድ መወስድና መተባበር፣ የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራስፎርሜሽን ምሰሶ ነው።
ኢትዮጵያ በኤአይ ዘርፍ ትብብር ከምታደርጋቸው ሀገራት ውስጥ በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ቻይና ነች።
እአአ በ2025 ሁለቱ ሀገራት በኤአይና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። እአአ በጥር 2026 ደግሞ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ ኢትዮጵያና ቻይና የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ከተለመዱት ዘርፎች ባሻገር ለማስፋፋት ተስማምተዋል። የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት ካደረጉ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ “በኢ-ኮሜርስ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ በአረንጓዴ ልማትና በምርምርና ፈጠራ” ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተወያይተዋል።መግለጫው ሀገራቱ በጋራ የወደፊት እጣፈንታ ላይ የተመሰረተ በሁኔታዎች የማይቀየር ስትራቴጂካዊ አጋርነት (all-weather partnership) ለመገንባት ቃል ገብተዋል።
የሀገራቱ ትብብር ወደ ተቋማት ተሸጋግሮ ፍሬ የትብብር ፍሬ አፍርቷል።የኢትዮጵያ ኤአይ ኢንስቲትዩት ከቻይና መንግስት ተቋማት፣ ዩኒቨርስቲዎችና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር የኤአይ ምርምር፣የዲጂታል ኢኖቬሽንና የሰው ኃይል ልማት ለማምጣት የሚያስችል ጥምረት መፍጠር ችሏል።ቻይና በኤአይ ዘርፉ ያላት አለምአቀፍ መሪነትና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጥረት በመደገፍ ያካበተችው ሰፊ ልምድ ሌሎች ሊማሩበት የሚገባ ነው።
ቻይና በአለም ቀዳሚ የሆኑ የኤአይ ኩባንያዎች፣ የምርምር ተቋማትና የፈጠራ ምህዳር መገኛ ስትሆን በ5ጂ ኔትዎርክ፣ በክላውድ ኮምፑቲንግ፣ በዳታ ማዕከል ግንባታ እና ለኤአይ እድገት አስፈላጊ በሆነው ከፍተኛ ፍጥነት ባለው ኮምፑቲንግ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አድርጋለች። በእነዚህ ምክንያቶች ኢትዮጵያ በኤአይ ዘርፉ ከቻይና ጋር መተባበሯ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያስገኝላት ነው።

ከቴክኖሎጂ ልማት በተጨማሪ ቻይና በኤአይ አስተዳደር (AI Governance) ዘርፍም ጉልህ ልምድ አላት። የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ በሻንጋይ በተካሄደው የ2026ቱ አለምአቀፍ የኤአይ ስብሰባ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር የኤአይ ቴክኖሎጂ በፍጥነት እያደገ መሄዱን፣ ብዙ እድሎችን እንዲሁም ከአስተዳደር ጋር የተያያዙ ፈተናዎችን ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ሺ “በቻይና እይታ፣ ሁሉም ሀገራት ሰውን ማዕከል ያደረገ አቀራረብ በመከተል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) ለበጎ ዓላማና ለሰብዓዊ ጥቅም ማልማት ይገባቸዋል። ኤአይ ለጋራ ብልጽግናና ለጋራ ደህንነት አስፈላጊ አንቀሳቃሽ ኃይል እንዲሆን ማረጋገጥ አለብን። ፍትሃዊና ሚዛናዊ የዓለም አቀፍ የኤአይ አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት በጋራ መስራት ይኖርብናል” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሺ አክለውም እንደገጹት ቻይና በኤአይ አስተዳደር ዙሪያ ግልጽነት የተሞላበት አለምአቀፍ ትብብር እንደሚያስለፍግና የአለምን ስልጣኔ በማይሸረሽር መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ትሻለች።

ቻይና በቁጥጥር፣ በመረጃ ደኅንነት እና በኤአይ ሥነ ምግባር ዙሪያ ያበረከተችው ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣል። ኢትዮጵያ የራሷን ሕጋዊና ተቋማዊ ሁኔታ የሚመጥን የኤአይ አስተዳደር ሥርዓት እንድታዳብርና ፈጠራን ከተገቢ ቁጥጥር ጋር ለማመጣጠን እንድትችል ይረዳታል። በመሆኑም ይህ አጋርነት ለኤአይ ልማት ብቻ ሳይሆን ውጤታማ የአስተዳደር ሥርዓትን ለመገንባትም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
ቻይናና ኢትዮጵያ በኤአይ ላይ ያላቸው ትብብር ከመሰረተልማት ዝርጋታ ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የቴክኖሎጂ አስተዳደር አድጓል። ይህ ጥምረት ኢትዮጵያ የኤአይ ልማቷን እንድታፋጥን፣ ተቋማዊ አቅሟን እንድታጠናክር በአለምአቀፍ የኤአይ አስተዳደር ላይ ሚና እንዲኖራት አስተዋጽኦ ይኖረዋል።











