የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ ያለው ህወሓት የፌደራል መንግስት ዛሬ(ነሐሴ 14፣2018) ጠዋት በመቀሌ ከተማ በሁለት ቦታዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽሟል ሲል ከሷል።
ህወሓት በፌስቡክ ገጹ ባጋራው መግለጫ የመጀመሪያው ጥቃት የተፈጸመው በመቀሌ ከተማ ሓውልቲ ክፍለከተማ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በኩሓ ክፍለከተማ መሆኑን ገልጿል። በመጀመሪያው ጥቃት 13 ሰዎች ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውን የጠቀሰው መግለጫው በሁለተኛው ጥቃት የደረሰ ጉዳት እንደሌላ ገልጿል።
የፌደራል መንግስት በዚህ ጉዳይ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም።
በህወሓትና የፈደራል መንግስት መካከል ያለው ፍጥጫ፣ ህወሓት የሁለቱን አመት ደምአፋሳሽ ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የተቋቋመውን እና በፌደራል መንግስት የሚደገፈውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እውቅና ከነፈገና ካፈረሰ በኋላ ከፍተኛ ደረጇ ላይ ደርሷል።
የፌደራል መንግስት ጥቃት ስለመፈጸሙ በይፋ ያለው ባይኖርም፣ ህወሓት ግን የድሮን ጥቃት እየተፈጸመበት እንደሆነ በመግለጽ ላይ ነው። ሁለቱ ወገኖች በሚቆጣጠሯቸው የሚዲያ ተቋማት የሚወጡ ዘገባዎችም ውጥረቱ ወደ ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት የሚፈጥሩ ናቸው።









