የኢትዮጵያ መንግሥት ስድስት የሱዳን ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቱን ሮይተርስ ስሙን ያልጠቀሰውን ባለሥልጣን ጠቅሶ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ይህን እርምጃ የወሰደችው፣ ሱዳን አዲስ አበባ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን (RSF) እየረዳች ነው የሚል ክስ ማቅረቧን ተከትሎ ነው።
ኢትዮጵያ በበኩሏ፣ ሱዳን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጦር ጋር በድጋሚ ግጭት ውስጥ የገባውን ህወሓትን እየደገፈች ነው የሚል ክስ አቅርባለች። ይሁን እንጂ ሁለቱም ሀገራት በእርስ በርስ ላይ የሚያቀርቡትን ክስ ያስተባብላሉ።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ይህ ውጥረት ወደ ጦርነት እንዳያመራና በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ቀውስ የበለጠ እንዳያባብስ ስጋት ፈጥሯል።
ሱዳን ባለፈው እሁድ የኢትዮጵያ መንግሥት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከግዛቷ ተነስቶ በሲቪል መሠረተ ልማት ላይ የአጥፍቶ ጠፊ ድሮን ጥቃት እንዲፈጽም ፈቅዳለች ሲል፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲሁም ለአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ቅሬታ ማቅረቡን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በአሶሳ የሚገኘው የሱዳን ቆንስላ ስድስት ሠራተኞች በ48 ሰዓታት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ማድረጓን የጠቀሰው ዘገባው፣ ባለሥልጣኑ ምክንያቱን ግልጽ አለማድረጋቸውን ገልጿል።
ኢትዮጵያ ሱዳን፣ ኤርትራና ግብጽ ህወሓትን ጨምሮ በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን በመርዳት ትከሳለች። ሦስቱም ሀገራት ክሱን ያስተባብላሉ።










