አሜሪካ ደቡብ አፍሪካንና ሩዋንዳን እ.ኤ.አ. ከጥር 1 ቀን 2027 ጀምሮ ከሰሃራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ከቀረጥ ነፃ የንግድ ፕሮግራሟ (AGOA) ልታግድ መሆኗን አስታወቀች። ይህ ውሳኔ ወደ አሜሪካ የሚላኩ የደቡብ አፍሪካ የመኪና መለዋወጫዎችንና ወይን ጠጅን እንዲሁም የሩዋንዳ ቡናን የሚጎዳ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ጀሚሰን ግሬር ሰኞ ዕለት ሁለቱ ሀገራት ከአፍሪካ ዕድገትና ዕድል ሕግ (AGOA) እንደሚወገዱ ለኮንግረሱ አሳውቀዋል። ለውሳኔውም የሰብዓዊ መብት፣ የሙስናና የአሜሪካን ብሔራዊ ደህንነትና የውጭ ፖሊሲ ጥቅሞች የሚጻረሩ ጉዳዮችን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል።
እ.ኤ.አ. በ2000 የተቋቋመው AGOA ብቁ ለሆኑ የአፍሪካ ሀገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ያለቀረጥ እንዲልኩ ዕድል ይሰጣል። ደቡብ አፍሪካ ከፕሮግራሙ ትልቁን ጥቅም ያገኘች ሀገር ስትሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2025 በፕሮግራሙ ስር ወደ አሜሪካ የላከቻቸው ምርቶች ዋጋ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
“ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሩዋንዳና የደቡብ አፍሪካ መንግሥታት ከAGOA የብቁነት መስፈርቶች ጋር የማይጣጣሙ ተግባራትን እየፈጸሙ መሆኑን ወስነዋል” ሲሉ ግሬር በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ደቡብ አፍሪካ ነጭ ዜጎቿን እያሳደደች ነው በሚል ክስ በተደጋጋሚ አቅርቧል፤ ፕሪቶሪያ ግን ክሱን ትክዳለች። ዋሽንግተን ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ በዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት ያቀረበችውን የዘር ማጥፋት ክስ ጨምሮ የውጭ ፖሊሲዋንም ተችታለች።
የሩዋንዳ ከፕሮግራሙ መታገድ በምሥራቅ ዴሞክራሲያዊ ኮንጎ ከሚካሄደው ግጭት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተንታኞች ይገምታሉ። ዋሽንግተን ኪጋሊ የM23 አማጺያንን ትደግፋለች በሚል ትከሳለች። አሜሪካ በቅርቡ በሩዋንዳ መከላከያ ሚኒስቴርና በሌሎች ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ሩዋንዳ እ.ኤ.አ. ከ2018 ጀምሮ በAGOA ስር በልብስ ምርቶቿ ላይ ከፊል እገዳ ተጥሎባት ቆይቷል።የደቡብ አፍሪካ የንግድ ሚኒስቴር በውሳኔው የሚጎዱ የኢኮኖሚ ዘርፎችን እንደሚደግፍና ከአሜሪካ ጋር ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማስፋት እንደሚቀጥል ገልጿል። በAGOA ስር የሚላኩ ምርቶች ወደ አሜሪካ ከሚላከው አጠቃላይ ምርት 10 በመቶ ያህሉን፣ ከዓለም አቀፍ ወደ ውጭ ምርት ሽያጭዋ ደግሞ 1 በመቶ ብቻ እንደሚሸፍኑ አስታውቋል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳም ሀገራቸው አዳዲስ የኤክስፖርት ገበያዎችን ለማግኘት ጥረት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።
የሁለቱ ሀገራት መታገድ ዋሽንግተን ከፕሪቶሪያና ኪጋሊ ጋር ባላት የንግድ ግንኙነት ላይ ተጨማሪ ውጥረት የሚፈጥር ሲሆን፣ አሜሪካ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት ተመራጭ የንግድ ግንኙነት ወደፊት ምን አቅጣጫ እንደሚይዝ ጥያቄ አስነስቷል።











