ወደስልጣን ተመልሷል የተባለው ምክርቤት ደብረጽዮንን የትግራይ የክልል ፕሬዚደንት አድርጎ መረጠ

tplf-debretsion

በእነ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት የነበረውን የትግራይ ክልል ምክርቤት ወደ ስልጣን መመለሱን ከገለጸ ከሁት ሳምንት በኋላ በዛሬ እለት የክልል ፕሬዚዳንት፣ የዋናና ምክትል አፈጉባኤ ምርጫ ማድረጉን አስታውቋል።

ህወሓት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ ዶክተር ደብረጽዮን በአብለጫ ድምጽ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል ብሏል።

በፌደራል መንግስት እውቅና ያለውና በጄነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ህወሓት ፈርሶ የነበረውን ምክርቤት ወደ ስልጣን ለመመስ ያሳፈውን ውሳኔ ግጭት ቀስቃሽ ነው ሲል በጽኑ ማውገዙ ይታወሳል።

ጀነራል ታደሰ የህወሓት እርምጃ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስና በክልሉ ሌላ ዙር ጦርነት የሚቀሰቅስ ነው ነበር ያሉት።

በ2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰውና ለሁለት አመታት የቆየው ደምአፋሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተቋጨ በኋላ ህወሃትና የፌደራል መንግስት ክልሉን የሚያስተዳድር አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያቋቁሙ ተስማምተው ነበር። ነገርግን በተይም ህወሃት ወደ ሁለት ጎራ ከተከፋፈለ በኋላ በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት ለጊዜያዊ አስተዳደር እውቅና ነፍጓል፤ ከፌደራል መንግስቱም ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቷል።

የፌደራል መንግስትና ህወሓት አንደኛቸው ሌላኛቸውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ነጥቦች ባለማክበርና በመጣስ መወነጃጀል የጀመሩት የስምምነቱ አንደኛ አመት ሲከበር ጀምሮ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ተባብሶ ቀጥሏል

የፌደራል መንግስት የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ባለስልጣናት ከኤርትራ መንግስት ጋር በማበር በኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲኖር እየሰሩ ነው የሚልም ጠንካራ ክስም ማቅረቡ ይታወሳል

Share this article

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *