የሊቢያ ጦር ሃይል ዋና አዛዥ መሀመድ አሊ አህመድ አል ሃዳድ በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ አቅራቢያ በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸው አልፏል።
ሲጓዙበት የነበረው ጀት ከቱርክ ተነስቶ ወደ ሊቢያ በመብረር ላይ ነበር።
የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ይርሊካያ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንደገለጹት የጦር አዛዡ የተሳፈሩበት አውሮፕላን ከአንካራ ኢሰንቦጋ አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ ትሪፖሊ መጓዝ እንደጀመረ የሬዲዮ ግንኙነት ከ40 ደቂቃ በኋላ ቋረጡን ተናግረዋል።
ባለሥልጣናቱ የአውሮፕላኑን ፍርስራሽ በአንካራ አቅራቢያ በምትገኝ መንደር ውስጥ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ግንኙነቶች ከመቋረጣቸው በፊት አውሮፕላኑ አየር ላይ እያለ በገጠመው ብልሽት ምክንያት ድንገተኛ ማረፊያ ጠይቆ እንደነበርና አውሮፕላኑ ወደተነሳበት አየር ማረፊያ እንዲመለስ ተደረጎ እዚያም ለማረፍ ዝግጅት እንደጀመረ ተናግዋል። አውሮፕላኑ ለማረፍ በዝግጅት ላይ በነበረበት ቅጽበት ከራዳር መጥፋቱን የገለጹ ሲሆን በኋላ የወጣ ቪዲዮ ያስቀረው ምስል ሰማይ ላይ ፍንዳታ የሚመስል ብልጭታ ያሳያል።
የአደጋው ዝርዝር ሁኔታ
- የአውሮፕላኑ ዓይነት፦ ዳሶ ፋልኮን 50 (Dassault Falcon 50) የግል ጄት ሲሆን፣ በማልታ የተመዘገበና በኪራይ የሚያገለግል እንደሆነ ተገልጿል።
- መነሻና መድረሻ፦ ከአንካራ ኢሰንቦጋ አውሮፕላን ማረፊያ (Esenboğa Airport) በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2፡10 ላይ ተነስቶ ወደ ትሪፖሊ በመጓዝ ላይ ነበር።
- የአደጋው መንስኤ፦ አውሮፕላኑ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የኤሌክትሪክ ብልሽት እንዳጋጠመውና ድንገተኛ ማረፊያ (Emergency Landing) እንዲፈቀድለት ለተቆጣጣሪዎች ማሳወቁ ተነግሯል። ሆኖም ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ለመመለስ በሚሞክርበት ወቅት በምሽቱ 2፡52 ላይ ከራዳር ጠፍቷል።
- የወደቀበት ቦታ፦ የአውሮፕላኑ ፍርስራሽ ከአንካራ በስተደቡብ 70 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው ሀይማና (Haymana) በተባለች ወረዳ ኬሲካቫክ መንደር አቅራቢያ ተገኝቷል።
በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈ ከፍተኛ መኮንኖች
በአደጋው የጦር አዛዡን ጨምሮ በአጠቃላይ ስምንት ሰዎች (አምስት የሊቢያ ልዑካን እና ሦስት የበረራ አባላት) መሞታቸው ተረጋግጧል። ከሟቾቹ መካከል፦
- ሌተናል ጄኔራል መሐመድ አሊ አል-ሐዳድ – የሊቢያ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም
- ሜጀር ጄኔራል አል-ፊቱሪ ግራቢል – የሊቢያ የምድር ጦር አዛዥ
- ብሪጋዴር ጄኔራል ማሕሙድ አል-ቃታዊ – የሊቢያ ወታደራዊ ማኑፋክቸሪንግ ባለሥልጣን ዳይሬክተር
- መሐመድ አል-አሳዊ ዲያብ – የኤታማዦር ሹሙ አማካሪ
- መሐመድ ዑመር አሕመድ ማሕጁብ – ወታደራዊ ፎቶግራፍ አንሺ
የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ሀሚድ ዲበይባህ “ይህ ትልቅ አሳዛኝ አደጋ ለአገር፣ ለወታደራዊ ተቋሙ እና ለመላው ህዝብ ትልቅ ኪሳራ ነው… አገራቸውን በቅንነት እና በትጋት ያገለገሉ እና የዲሲፕሊን፣ የኃላፊነት እና የብሔራዊ ቁርጠኝነት ምሳሌ ናቸው።” ብለዋል።
መሀመድ አሊ አህመድ በምእራብ ሊቢያ ከፍተኛ የጦር አዛዥ የነበሩ ሲሆን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አደራዳሪነት አገሪቱን አንድ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ናቸው።
በኔቶ መሪነት የተቀጣጠለውን ሙአመር ጋዳፊን ከስልጣን ያወረደውን እና የገደለውን አመጽ ተከትሎ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2014 የተከፋፈለች ሊቢያን አንድ ለማድረግ በሚደረገው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አደራዳሪነት ሲካሄድ በነበረ ጥረት ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። ዋና አዛዡ በምእራብ ሊቢያ ከፍተኛ የጦር አዛዥ ነበሩ።
በአደጋው የሞቱት ሌሎች አራት ዋና ዋና መኮንኖች ሲሆኑ የሊቢያ ልዑካን በአንካራ ቱርክ የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ትብብር ለማሳደግ ያለመ ከፍተኛ የመከላከያ ድርድር ለማድረግ ተጉዘው እንደነበር የቱርክ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
በትሪፖሊ የሚገኘው የአብዱል ሀሚድ ዲቤይባህ የተባበሩት መንግስታት እውቅና ያለው የብሄራዊ አንድነት መንግስት በመላ ሀገሪቱ ለሶስት ቀናት ይፋዊ ሀዘን አውጇል።
እስካሁን ባለው መረጃ አደጋው በጥቃት ሳይሆን በቴክኒክ ችግር ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ የቱርክ ባለስልጣናት የገለጹ ሲሆን የአንካራ ዋና አቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል። የሊቢያ መንግስትም የአደጋውን ምርመራ በተመለከተ ከቱርክ ባለስልጣናት ጋር ለመስራት ቡድን ወደ አንካራ ላኩ ተገልጿል።
የጦር አዛዦቹ የተሳፈሩበት ጄት በኪራይ የተገኘ የማልታ አውሮፕላን መሆኑን እና ባለሥልጣናቱ የባለቤትነት መብቱን ወይም የቴክኒክ ታሪኩን በተመለከተ በቂ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
መሐመድ አሊ አህመድ አል-ሃዳድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2020 ጀምሮ የሰራዊቱ ዋና አዛዥ ሆነው የተሾሙት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ አል-ሳርራጅ ነበር። ከምስራቃዊ ሊቢያ ጋር ስምምነት በመፍጠር የተከፋፈለች ሊቢያን አንድ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ተሰፋ የተጣለባቸው ሰው ነበሩ።
መረጃው የተገኘው ከአልጄዚራ ነው













