Loading...

ከ “ሐር የጤና መንገድ” ወደ ክልላዊ የህክምና ማዕከልነት- አዲስ አበባ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ የሆነችው ለምንድነው?

PetroChina Africa Regional Medical Evacuation and Treatment Center

በቅርቡ ቻይና በአፍሪካ ፈጣን የህክምና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ማዕከል በአዲስ አበባ አቋቁማለች። ይህ ማዕከል ፔትሮቻይና የአፍሪካ ክልላዊ የህክም ማዛወሪያ እና ህክምና መስጫ ማዕከል (PetroChina Africa Regional Medical Evacuation and Treatment Center) ይሰኛል።

የማዕከሉ መከፈት ቻይና በአፍሪካ ውስጥ እያደረገች ያለው ስትራቴጂካዊ ተሳትፎ ማደጉን የሚያሳይና “የጤና ሐር መንገድ” የተባለው ፕሮጀክት ቀጣይ ምዕራፍ መጀመሩን የሚያበስር ነው። ይህ እምርጃ ቻይና በጤና ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም በውጭ ሀገር ያሉ ሰራተኞቿን ጤንነ ትና ኢንቨስትመንቷን ለመጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ለዚህ ደግሞ በቻይና ወሳኝ መዳረሻ ሆና የተመረጠችው የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ነች።

ይህ ማዕከል 23 የአፍሪካ ሀገራትን እና በመላው አህጉሪቱ የሚሰሩ 5000 ገደማ የሚሆኑ ቻይናውያን ያገለግላል።የአደጋ ጊዜ ሕክምና፣ የሕክምና ግምገማ፣ የሕክምና ማዛወሪያ አገልግሎት፣ የጽኑ ሕሙማን እንክብካቤ፣ ማገገሚያ እና ወደ ሀገር መመለስን በአንድ የተቀናጀ ቦታ በማድረግ፣ የቻይናን ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅም ትርጉም ባለው መልኩ ያጠናክራል። ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ቀውስ ከተከሰተ በኋላ ብቻ ሕክምና የማደራጀት አሠራርን ወደ ቀድሞ ዝግጁነትና ቋሚ የክልላዊ አቅም ግንባታ የማሸጋገር እቅድ አካል ነው።

ይህ ማዕከል የስራተኞችን ደህንነት ከመጠበቅ የተሻገር ጠቀሜታ አለው። ለቻይና የሰራተኞችን ደህንነት መጠበቅ ማለት የኢኮኖሚ ደህንነትና ኢንቨስትመንትን በቀጣይነት ከማረጋገጥ ጋር በቀጥታ የተያያዘ  ነው።

ቻይና የፈጣን ምላሽ ማዕከልን ለማቋቋምና አገልግሎቱን ለመስጠት አዲስ አባባን ማዕከል አድርጋ መርጣለች። ቻይና ይህን ማዕከል የከፈተችው የአዲስ አበባን የአፍሪካ ማዕከልነትና ስትራቴጂካዊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫና ዋና የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነቸው አዲስ አበባ የጤና ዘርፍ ትብብሮችን ለመፍጠር ምቹ ነች። ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ የበረራ ትስስር በመፍጠር ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየርመንገድም አዲስ አበባን ለሕክምና በረራና እና ለአደጋ ጊዜ ሕክምና ቅንጅት በቻይና ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል።

ይህ አዲስ አበባ የዲፕሎማሲና የአቪዬሽን ማዕከል ከመሆን ወደ ክልላዊ የጤናና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ማዕከልነት እየተሸጋገረች መሆኗን ይህ ማዕከል ያሳያል። ለኢትዮጵያ ይህ እድል በቀላሉ ሊታለፍ አይገባም። ማዕከሉ የቻይና ኩባንያዎችን ሠራተኞች ለማገልገል የተቋቋመ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ሆስፒታሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የአደጋ ጊዜ ሕክምና ተቋማት ጋር ትስስር ቢፈጠር ለሀገሪቱ የጤና ሥርዓት ትልቅ አቅም ሊፈጥር ይችላል። የሙያ ሥልጠና፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአደጋ ጊዜ ሕክምና እና የጉዳት ሕክምና አቅም ማሳደግ ሊገኙ ከሚችሉት ጥቅሞች መካከል ናቸው።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ይህንን ማዕከል በአዲስ አበባ መገኘቱን እንደ አንድ የውጭ ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን፣ የክልላዊ የጤና አገልግሎት አቅሟን ለማጠናከር እንደ ስትራቴጂያዊ እድል ልትጠቀምበት ይገባል። በተለይም አዲስ አበባ በዲፕሎማሲ፣ በአቪዬሽንና በሎጂስቲክስ ያላትን ጠንካራ አቅም ከጤና አገልግሎት ጋር ማጣመር ከተቻለ፣ ከአፍሪካ ዋና የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ባሻገር የክልሉ የሕክምናና የአደጋ ጊዜ ምላሽ ማዕከል ልትሆን ትችላለች

በአጠቃላይ ማዕከሉ ቻይና ከኢትዮጵያ በመነሳት በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ለሚሰሩ ዜጎቿ በቀላሉ ፈጣን የህክምና ምላሽ እንድትሰጥ የሚያስችል ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ማዕከሉን በማስተናገዷ የፈጣን ህክምና ምላሽ ልምዶችን እንድትቀስም መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላታል። የማዕከሉ መቋቋም የኢትዮጵያና ቻይና ዘላቂ የሁለትዮሽ ትብብር (all weather partnership) እየሰፋ መሄዱን እንዲሁም ኢትዮጵያ፣ ቻይና በአፍሪካ ለምታካሂደው ትብብር  ወሳኝ አጋር እየሆነች መምጣቷን የሚያሳይ ነው

Share this article

Subscribe

By pressing the Subscribe button, you confirm that you have read our Privacy Policy.
Your Ad Here
Ad Size: 336x280 px

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው