ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በዛሬው እለት ጅቡቲ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፌስቡክ ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ጁቡቲ ሲደርሱ የጅቡቲ አቻቸው እስማኤል ኦማር ጉሌ እንደተቀበሏቸው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሁለቱ መሪዎች በቀጠናዊ ሰላምና በጂኦፖለቲካዊ ክስተቶች እንዲሁም በሁለትዮሽ የንግድ፣ ጀሎጂስቲክና የልማት ጉዳዮች ላይ ወያይተዋል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዑክ ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የፋይናንስ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ሁሴን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ መካተታቸው የጉዞውን ከፍተኛ ስልታዊ ጠቀሜታ ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ጁቡቲ ያቀኑት እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን እውቅና ተከትሎ በቀጠናው አዲስ ክስተት ከተፈጠረ ከሁለት ሳምንታት ገደማ በኋላ ነው።
በአለም ወሳኝ በሚባለው የማሪታይም መስመር ላይ የምትገኘው ጁቡቲ የእስራኤልን እውቅና በማውገዝ፣ የሶማሊላንድ የዲፕሎማቶችን አባራለች። ጁቡቲና ሌሎች ሀገራትና አለምአቀፍ ድርጅቶች የእስራኤልን እርምጃ የተቃወሙት ሶማሊላንድ የግዛቴ አካል ነች ለምትለው ሶማሊያ ድጋፍ ለመስጠት ነው። ነገርግን ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ አቋሟን በይፋ አላሳወቀችም፤ ሁለቱ መሪዎች በዚህ ጉዳይ ስለመምከራቸው የታወቀ ነገር የለም።
ጠረፋማዋ ጁቡቲና እና ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ አንዳቸው ለሌላኛው ጥገኛ የሚባል መስተጋብ ነው ያላቸው። ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የወጭና ገቢ ንግድ የሚመላለሰው በጅቡቲ ወደቦች ሲሆን የወደብ ኪራይና ተያያዥ ክፍያዎች የጂቡቲን 25 በመቶ ገደማ የሀገር ውስጥ ገቢ(GDP) ይሸፍናሉ።

የቀጠናው ውጥረት፦ የግብፅ እና የሶማሊላንድ ጉዳይ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝት የመጣው ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተጽዕኖ ለማስፋት በጅቡቲ እና በኤርትራ የወደብ ልማት ላይ ለመሳተፍ ስምምነት ባደረገችበት ወቅት ነው። የካይሮ ይህ እንቅስቃሴ በናይል ውኃ አጠቃቀም ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ባለባት አለመግባባት በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ እና ስልታዊ ጫና ለመፍጠር የታለመ እንደሆነ ተንታኞች ይገልጻሉ። ይህም ለኢትዮጵያ ጅቡቲን ከንግድ አጋርነት ባለፈ ለብሔራዊ ደኅንነቷ ወሳኝ ያደርጋታል።











