Loading...

የኢትዮጵያ ድል በሌጎስ፦ ዊሃ፣ ቬሮኒካ አዳነ እና ሃዲንቆ የአፍሪካ የሙዚቃ ሽልማትን (AFRIMA 2026) ድል ተቀዳጁ

ባለፈው እሁድ ጥር 11 ቀን 2026 በናይጀሪያ ሌጎስ በተካሄደው 9ኛው የኦል አፍሪካ ሙዚቃ አዋርድ (AFRIMA) ላይ የኢትዮጵያ አርቲስቶች ደምቀው ውለዋል። በዝግጅቱ ላይ ኢትዮጵያውያን በዕጩነት ቀርበው የነበረ ሲሆን፣ ድምፃዊት ዊሃ (Weeha) ፣ ድምፃዊት ቬሮኒካ እና አርቲስት ሃዲንቆ (Haddinqo) ታላላቅ ሽልማቶችን ለአገራቸው በማስገኘት ታሪክ ሰርተዋል።

በዕለቱ እጅግ በጉጉት ሲጠበቁ ከነበሩት ዘርፎች መካከል በሆነው “ምርጥ የአፍሪካ ዳንስ/ኮሪዮግራፊ” (Best African Dance/Choreography) ዘርፍ፣ ወጣቷ ድምፃዊት ዊሃ “ዲማማ” (Dimama) በተሰኘው ስራዋ የዓለም አቀፍ ደረጃ አርቲስቶችን በመብለጥ አሸናፊ ሆናለች። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አርቲስት ሃዲንቆ ደግሞ በ “ምርጥ የአፍሪካ ጃዝ” (Best African Jazz) ዘርፍ አሸናፊ በመሆን የኢትዮጵያን የሙዚቃ ልዕልና በአህጉሪቱ መድረክ ላይ አረጋግጧል። ቬሮኒካ አዳነ ደግሞ “ካንተ ሌላ” በሚለው ስራዋ በምርጥ የአፍሪካ ባህላዊ ሙዚቃ ዘርፍ አሸናፊ ስትሆን፣ በሌጎስ በነበረው መድረክ ላይ ያቀረበችው ትርኢት የኢትዮጵያን ባህልና ዜማ ለዓለም ያስተዋወቀ ነበር።የኢትዮጵያን ባህላዊ ውዝዋዜና ዜማ ከዘመናዊ የሙዚቃ ቅንብር ጋር በማዋሃድ ያቀረቡት ዝግጅት በሌጎስ ተገኝቶ የነበረውን ታዳሚ በአድናቆት አስነስቷል።

ከአሸናፊዎቹ በተጨማሪ ሌሎች የኢትዮጵያ አርቲስቶችም በዕጩነት ተካተው የነበረ ሲሆን፣ ያሬድ ነጉ በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ወንድ አርቲስት፣ እንዲሁም ሃሌሉያ ተክለጻዲቅ፣ ማህሌት ወንድሙ፣ ሳሌምያ እና ዊሃ በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ሴት አርቲስት ዘርፍ ለአገራቸው ክብር ተፎካክረዋል። ምንም እንኳን እነዚህ ዘርፎች በታንዛኒያው ጁማ ጁክስ እና በማዳጋስካሯ ዴኒስ ቢወሰዱም፣ የኢትዮጵያ አርቲስቶች በተለያዩ ዘርፎች በብዛት መታጨታቸው የኢትዮጵያ ሙዚቃ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ደረጃ ያለውን ከፍተኛ ተፅዕኖ በግልጽ ያሳየ ክስተት ሆኖ አልፏል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው