በአሜሪካ በተከሰተው ከባድ የበረዶ አውሎንፋስ ምክንያት እስከ ኒው ሜክሲኮ ግዛት ድረስ ከ670,000 በላይ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸው ሲሆን 10,000 የሚደርሱ በረራዎች ደግሞ በስጋት በዛሬው እለት መቋረጣቸው ተዘግቧል። የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በረዶ፣ በረዷማ ዝናብ፣ ቀዝቃዛ ዝናብና ከፍተኛ ቅዝቃዜ 2/3ኛ በሚሆነው የሀገሪቱን ምስራቃዊ ክፍል ከዛሬ ጀምሮ ለሳምንት ያህል ሊቆይ ይችላል።
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት 17 ግዛቶችና የኮሎምቢያ ዲስትሪክት አስቸኳይ የአየር ንብረት አዋጅ ማወጃቸውን አስታውቋል። የመስሪያ ቤቱ ጸኃፊ ክሪስቲ ኖይም አሜሪካውያን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

“በጣም፣ በጣም ቀዝቃዛ ነው የሚሆነው። ስለሆነም ሁሉም ሰው ነዳጅና ምግብ እንዲያከማች እናበረታታለን፤ አብረን እናልፈዋለን” ብለዋል ኖይም።
ኃይል የተቋረጠባቸው ሰዎች ቁጥር በመጨመር ላይ ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ ግን ከ670,000 በላይ ማለፉን የፓወር አውቴጅ መረጃ ያመለክታል።
በሚኒሶታ, በቴክሳስ፣ በቴነሴና በሎይዚያና ግዛቶች በእያንዳንዳቸው ከ100,000 በላይ ሰዎች ከኃይል አቅርቦት ውጭ ሆነዋል። ኬንተኪ፣ ጆርጂያ፣ ቨርጂኒያና ኒው ሜክሲኮ የተባሉት ሌሎች ግዛቶችም ከተጠቁት ግዛቶች መካከል ይገኙበታል።
ዴልታና ጄትብሉን ጨምሮ ዋናዋናዎቹ የአሜሪካ አየር መንገዶች፣ ተጓዦች ለድንገተኛ የበረራ ቅየራና ስራዛ ዝግጁ እንዲሆኑ አስጠንቅቀዋል።













