Loading...

ባንኮች ያለ ቪዛና የጉዞ ቲኬት ለደንበኞቻቸው እስከ 20ሺ ዶላር ክፍያ እንዲፈጽሙ ብሔራዊ ባንክ ፈቀደ

ብሔራዊ ባንክ በዛሬው እለት ይፋ ባደረገው የውጭ ምንዛሬ መመሪያ ማሻሻያ መሰረት ባንኮች የውጭ ተቋም በሚሰጠው ማረጋገጫና ደንበኛው በሚያቀርበው ጥያቄ ለአንድ ጉዳይ ከ20ሺ የአሜሪካን ዶላር ወይም ተመጣጣኝ የሌላ ሀገር ገንዘብ ያልበለጠ የውጭ ምንዛሬ ያለ ቪዛና የአውሮፕላን ቲኬት ክፍያ መፈጸም ይችላሉ።

ቀደም ሲል በነበረው መመሪያ ወደ ውጭ ሀገር ለትምህርት፣ ለህክምናና ለሌሎች ጉዳዮች ወደ ውጭ የሚሄዱ ኢትዮጵያዊውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ቪዛና የአውሮፕላን ቲኬት በእጃቸው መያዝ ይጠበቅባቸው ነበር።

የውጭ ምንዛሬ ገበያን ለማጎልበት ከባለፈው ሐምሌ 2016ዓ.ም ጀምሮ በውጭ ምንዛሬ መመሪያው ላይ ማሻሻያ እያደረገ መቀጠሉን የገለጸው ብሔራዊ ባንክ፣ ዛሬ ይፋ ያደረገው የመመሪያ ማሻሻያ ተጨማሪ 18 ነጥቦችን አካቷል።

ብሔራዊ ባንኩ ያወጣቸው ማሻሻያዎች ግለሰቦችን፣ ባንኮችን፣ የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎችን ኢንቨስተሮችንና ድርጅቶችን የሚመለከቱ ናቸው።

በማሻሻያው መሰረት የውጭ ምንዛሬ አካውንት ያለው ደንበኛ ለውጭ ሀገር ክፍያ የሚያገለግል አለምአቀፍ ካርድ እንዲኖረው፣ ለትዳር አጋርና ለልጆቹ የትምህርት፣ የህክምና የጉዞ ወጭ እንዲከፍልና ህጋዊ ሰነድ ለባንኮች በማቅረብ እስከ 3000 የአሜሪካን ዶላር ውጭ ላለ ዘመድ እንዲልክ የሚያስችል ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ ምንዛሬ አካውንት ለመክፈት ይጠየቁ የነበረው 100 ዶላርና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሆነ ግለሰብ ወደ ሀገር ውስጥ ይዞት በሚገባው የትኛውንም ያህል መጠን የውጭ ምንዛሬ ላይ ይጠየቅ የነበረው የጉምሩክ ባለቤትነት ማረጋገጫ ቀርቷል።

ግለሰቦች ከ10ሺ የአሜሪካን ዶላር በላይ ይዘው ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የጉምሩክ ማረጋገጫ ማቅረብ  ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን በአዲሱ መመሪያ ግን በቀጥታ “በባንኮችና ሕጋዊ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ቢሮዎች በኩል ወደ ብር መመንዘር አለያም ወደ የውጭ ምንዛሪ ሂሳብ በማስገባት ተቀማጭ ማድረግ ይችላል፡፡”

በማሻሻያው ድርጅቶች ከውጭ ንግድ የሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ሙሉ በሙሉ በሪቴንሽን ሂሳባቸው ያለ ምንም የጊዜ ገደብ እንዲይዙና ከውጭ ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ሳይጨምር በእርዳታ፣ በስጦታ ወይም ከሌላ ምንጭ የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የቁጠባና የጊዜ ገደብ የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲከፍቱ ይፈቅዳል። በተጨማሪ በውጭ ንግድ ላይ የተሰማራ ላኪ ድርጅት ከውጭ አካል ጋር የቅድመ ክፍያ ስምምነት ላይ በመድረስና ስምምነቱን ለላኪው ደንበኛ ባንክ በማቅረብ ቅድማ ክፍያ ይፈጸምለታል። በማሻሻያው መሰረት፣ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች የመዋእለ ነዋያቸውን ሁኔታ በብሔራዊ ባንክ እያስመረመሩ ከሀገር ውጭ በሌላ ሀገር መዋእለ ነዋያቸውን ፈሰስ ማድረግ ይችላሉ።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስተሮች፣ ኤምባሲዎችና በሀገር ውስጥ የሚሰሩ ዓለምአቀፍ ተቋማት የተራድኦ ድርጅቶችን ጨምሮ ያለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማረጋገጫ በባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሂሳብ እንዲከፍቱ መመሪያው ያስችላቸዋል።

ባንክችም ያለ ብሔራዊ ባንክ ማረጋገጫ የፎርዋርድ የውጭ ምንዛሬ ግብይት እንዲያደርጉና ከካፒታላቸው ከ10 በመቶ ያልበለጠ ለግሉ ዘርፍ የውጭ ሀገር ብድር ዋስትና መስጠት እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል።

የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች የሚይዙት ጥሬ የውጭ ምንዛሬ መጠን ቀደም ሲል ከነበረው የካፒታላቸው 10 በመቶ ወደ 25 በመቶ ከፍ እንዲልና አስፈላጊ ሰነድ ላሟላ ሰው ለቪዛ፣ ለፓስፖርትና ለፈቃድ እድሳት የውጭ ምንዛሪ እንዲሸጡ ተፈቅዶላቸዋል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው