Loading...

ምርጫ ቦርድ “አወዛጋቢ” ቦታዎችን በተመለከተ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ እንዳያደርግ በፍርድ ቤት በጊዜያዊነት ታገደ

የፌደሬሽን ምክር ቤት የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው “አወዛጋቢ” ቦታዎች የሚገኙ የምርጫ ክልሎች ከትግራይ ክልል ውጭ ሆነው የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ብቻ እንዲያካሄዱ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። 

ፌደሬሽኑ ውዝግቡ እስከሚፈታ ድረስ የሁመራ፣ የአዲረመጽ፣ የኮረም እፍላ፣ የጠለምትና የራያ አላማጣ የምርጫ ክልሎች የህዝብ ተወካዮች ምርጫ ብቻ እንደሚካሄድ ነበር የገለጸው።
በዚህ ውሳኔ መሰረት አካባቢዎቹ በየትኛውም ክልል ውስጥ ታቅፈው ምርጫ ስለማያካሄዱ፣ የክልል ምክር ቤት ተወካዮች ምርጫ አይካሄድም።

ምርጫ ቦርድም የፌደሬሽኑን ውሳኔ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ከትናንት በስትያ ማስታወቁ ይታወሳል።

ውሳኔው ስምረት ፓርቲን ጨምሮ በትግራይ የፖለቲካ ፖርቲዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን አማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) በአንጻሩ ውሳኔውን ደግፎ መግለጫ አውጥቷል።

በቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንትና በአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ስምረት የፌደሬሽኑን ውስኔ “ህገመንግስታዊ ስርአቱን የሚንድ” ሲል በጽኑ ማውገዙ ይታወሳል።

ፓርቲው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ቦርዱ ውሳኔው እንዳይፈጽም በጊዜያዊነት መታገዱን አቶ ጌታቸው በፌስቡክ ገጻቸው ያጋሩት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያሳያል።

ፍርድ ቤቱ የከሳሽ ክስና ማስረጃ በግልባጭ ለምርጫ ቦርድ እስኪደርስና ክርክሩ ታይቶ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ቦርዱ ውሳኔውን ተግባራዊ እንዳያደርግ አግዷል።

የይገባኛል ጥያቄ የተነሳባቸው አካባቢዎች ጥቅምት 24፣2013ዓ.ም በፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ህወሓት መካከል ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በትግራይ ክልል ስር ነበሩ። ይሁን እንጅ እነዚህ አካባቢዎች በኃይል ወደ ትግራይ ክልል እንደተካተቱና የማንነት ጥያቄ እንዳላቸው ጥያቄዎች ለረጅም ጊዜ ሲቀርቡ ቆይተዋል።

ጦርነቱን የቋጨው የፕሪቶሪያ ስምምነት እነዚህን ቦታዎች “አወዛጋቢ” (Contested area) የሚል አንቀጽ በማስገባት የየትኛውም ከልል ግዛት እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።

የፌደራል መንግስት የይገባኛል ውዝግቡ በህዝብ ውሳኔ በዘለቄታዊነት ይፈታል የሚል አቋም ይዟል።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው