Loading...

ሱዳን ኢትዮጵያን በድሮን ጥቃት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ከሰሰች

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ ድሮኖች እንዲታጠቁና ወደ ሱዳን ተኩሰው ጥቃት እንዲፈጽሙ ፈቅዳለች ሲል ከሰሰ።

ይህም ሱዳን ጎረቤቷን ኢትዮጵያን ለሦስት ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እጇ አለበት ስትል በቀጥታ ስትከስ የመጀመሪያዋ ያደርጋታል።

እንደ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ከሆነ በየካቲት እና በመጋቢት ወራት የተሰነዘሩት የድሮን ጥቃቶች የተቀነባበሩት ከኢትዮጵያ ግዛት በመነሳት ነው። ሱዳን እነዚህ ድሮኖች በሀገሪቱ ወታደራዊ እና ሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት ለማድረስ ጥቅም ላይ ውለዋል ብላለች።

ይህ ክስ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየውን የድንበር እና የህዳሴ ግድብ ውጥረትን ወደ ሌላ አደገኛ ምዕራፍ ሊያሸጋግረው እንደሚችል ተንታኞች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

የቀጣናው ስጋት

ሱዳን በጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው ጦር እና በጄነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) በሚመራው የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይል (RSF) መካከል በሚደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች። ሱዳን አሁን ያቀረበችው ክስ ኢትዮጵያ አንዱን ወገን እየረዳች ነው የሚል አንድምታ ያለው ሲሆን ይህም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ሰላም ላይ ጥላ አጥልቷል።

እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን በኩል ለቀረበበት ቀጥተኛ ክስ በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም። ሆኖም ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባና ሰላም እንዲሰፍን እንደምትሻ ስትገልጽ ቆይታለች።

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው