የቻይና-አፍሪካ ወዳጅነት ጠንክሮ መቀጠሉን ያረጋገጡት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እሁድ በሰጡት መግለጫ ቻይና ለ36 ተከታታይ አመታት በአፍሪካ ጉብኝት በማድረግ የዲፕሎማሲ አመት የመጀመር ልምድ እንዳላት አስታውሰዋል። ሚኒስትሩ እንደገለጹት ይህ የቻይናን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
“የቻይና እና አፍሪካ ወዳጅነት ከትውልድ ወደትውልድ እየተላለፈ የመጣ፣ በልብ ለልብ ግንኙት የጸና እንዲሁም
በላብና በደሞ የተገነባ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም” ሲሉ ተናግረዋል ዋንግ።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት የቻይና አፍሪካ ግንኙነት በ2026 ተከታታይ ለውጦችን ያሳያል።
የጋራ እጣፈንታ የሚጋራ የቻይና-አፍሪካ ማህበረሰብ ለመገንባት አዲስ እርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል ዋንግ። ዋንግ አክለውም በ2ዐ26 በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ቻይናን እንደሚጎበኙ፣ ለፈተና የማይገበር የርስበርስ መረዳዳታቸውን እንደሚያጠናክሩና ለጋራ እጣፈንታ አዲስ ምዕራፍ እንደሚተልሙ ተናግረዋል።


ቻይና ከመጭው ግንቦት 1 (ሜይ 1) ጀምሮ ለአፍሪካ ሀገራት ዜሮ ታሪፍ ተግባራዊ እንደምታደርግ የገለጹት ዋንግ “ቻይና ታሪፉን ሙሉ በሙሉ ያስወገደችው ንግድን ለመጨመር ህዝቡ የተሻለ ጥቅም እንዲያገኝና አፍሪካ ሰፊውን የቻይና ገበያ እንድታገኝ ለመርዳት ነው” ብለዋል።
የቻይና-አፍሪካ የባህል ልውውጥ አመት መጀመሩን ያስታወሱት ዋንግ በአመቱ 600 ገደማ ዝግጅቶችን ለማካሄድ እቅድ እንደተያዘ ጠቅሰዋል። ዋንግ እንዳሉት ቻይና ከአፍሪካ ወንድምና እህቶቿ ጋር የስልጣኔ ልውውጥ ለማድረግ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማሳደግና የቻይና-አፍሪካ ግንኙነት ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፉን ለማረጋገጥ ፈቃደኛ ነች ብለዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአፍሪካ ቻይና ግንኙነት በተጨማሪም ስለ ባለብዙ ወገን ግንኙነት(Multilateralism) እና ስለታይዋን ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ቻይና ለተለመደው በአሜሪካ ለሚመራው የምዕራባውያን የበላይት ፈጽሞ እንደማትገዛና ይልቁንም በመከባበር ላይ የተመሰረት የባለብዙ ወገን አለምአቀፍ ስርአት(World order) እንዲነብር እንደምትፈልግ ዋንግ ተናግረዋል። የአለም ሁኔታ እየተወሳሰበና ኃይል እየተበታተነ በመምጣቱ አንድ ሀገር የቱንም ያህል ጠንካራ ቢሆን አለምአቀፍ ችግሮችን መፍታት አይችልም ያሉት ዋንግ መፍትሄው ብዙ ሀገረት ወደ ግሎባል ገቭርናንስ ኢኒሼቲቭ(GGI) እንዲሳተፉ ማድረግ፣ “ተመድን ለማጠናከር መስራት፣ ተመድን መከላከልና ጠንካራ ማድረግ ነው” ብለዋል።
ቻይና አለም በጂኦፖለቲካዊ ጎራዎች ሳይሆን በተመድ መመራት አለባት የሚል የረጅም ጊዜ አቋም አላት። ለዚህም ነው ተመድን ከማፍረስ ይልቅ ማሻሻልና ማጠናከር በጣም የተሻለ አማራጭ አድርጋ የምታየው።
የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ
እስራኤልና አሜሪካ በመቀናጀት በኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ መካከለኛው ምስራቅ በቅርብ ጊዜ ታሪክ ታይቶ ወደማይታወቅ ትርምስ ውስጥ ገብቷል። ኢራን ለጥቃቱ የሰጠችው አጸፋ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ያሉባቸውን በርካታ የአረብና የባህረሰላጤው ሀገራት ሰለባ ማድረጉ፣ የግጭቱን አድማስ እጅግ ሰፊና አሳሳቢ አድርጎታል።
ቻይና ጥቃት ፈጻሚዎቹን እስራኤልና አሜሪካን የሚያወግዝ መግለጫ ካወጡ ሀገራት ውስጥ አንዷ ነች።

ዋንግ ዪ በዛሬው መግለጫቸው “ይህ ጦርነት መጀመር ያልነበረበት ነው፤ ማንንም አይጠቅምም” ብለዋል። “ኃይል የችግር መፍቻ መንገድ አይደለም። ወደ ጦርነት ማምራት ጥላቻና ቀውስ ነው የሚፈጥረው።”
ቻይና ችግሩ ከጣልቃገብነት ይለቅ በዲፕሎማሲ እንዲፈታ እንደምትፈልግ እየገለጸች ነው። የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀጣናው ካሉ በርካታ አካለት ጋር እየተወያየ መሆኑንና ንግግርን ለማበረታታት ወደ ቀጣናው ልዩ መልእክተኛ መላኩን መግለጹ ይታወሳል።
ታይዋን
ሚኒስትሩ ቻይና የራሷ ግዛት አካል አድርጋ የምታያትን ታይዋንን በተመለከተም የተለመደውን አቋም አንጸባርቀዋል። “ታይዋን ከጥንት ጀምሮ የቻይና አካል ነች። ሀገር አልነበረችም፤ አይደለችም። ወደፊትም አትሆንም” ብለዋል ዋንግ።












