Loading...

ለአፍሪካ ትልቅ እድል ይዞ የመጣው 15ኛው የቻይና የልማት እቅድ

ቻይና የልማት እቅዶቿን ግልጽ ያደረገችበትን 15ኛውን የአምስት አመት እቅድ በሀገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ስልጣን ባለው ናሽናል ፒፕልስ ኮንግረስ(NPC) አጸድቃ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።  እቅዱ ቻይና በፈጠራ ስራዎችና አለምአቀፋዊ ተወዳዳሪነትን በሚያሰፉ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረጓን የሚያሳይ ነው።

እቅዱ ለአስርት አመታት የቻይናን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ ቢሆንም አሁን ግን ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለመላው አለም ትብብሮችም እድል የሚሰጥ መሆኑን በቲንጉዋ ዩኒቨርሲቲ የቻይና የልማትና እቅድ ባለሙያ የሆኑት ሊ ዢ  ለቻይናው ሲጂቲኤን ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ባለሙያው ይህ እቅድ በተለይም ለቻይና የእስያና የአፍሪካ ወዳጆች ትልቅ እድል ይዞ የሚመጣ ነው ብለዋል
“ልንገርህ፤ ትልቅ እድል ነው የሚሆነው። 15ኛው የአምስት አመት እቅድ አብዛኛው ይዘቱ ክፍት ስለመሆን ነው የሚያትተው። ቻይና ክፍት ትሆናለች፤ ከአለም ጋር ትተባበራለች።” 

ቻይና ከፍተኛ ፍጆታ ያለውን ገበያዋን ክፍት በማድረግ፣ የአፍሪካ ሸቀጦች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ እድል በመስጠትና ባቡርን ጨምሮ መሰረተልማቶችን በመገንባት፣ የእስያና አፍሪካ ወዳጆቿ እንዲጠቀሙ እንደምታደርግ ባለሙያው ዢ ይገልጻሉ። ቻይና በቀጣይ አምስት አመታ ውስጥ ለተጨማሪ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ከቀረጥ ነጻ እድል የምትሰጥ ሲሆን በዚህም የኢትዮጵያ ቡና፣ የኬንያ አቮካዶ፣ የቬትናም ባሳ አሳና የታይላንድ ዱሪያንስ በዝቅተኛና ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ ወደ ቻይና ገበያ ይገባሉ።

ቻይናውያን ደንበኞች ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የግብርና ምርቶች ለመግዛት ፍላጎት እያሳዩ በመሆናቸው በቀጣይ አምስት አመታት የአፍሪካና የእስያ የግብርና ምርቶችን በቻይናውያን የምግብ ጠረንጴዛዎች ላይ ልናገኛቸው እንችላለን። ይህ እንዲሳካ የአፍሪካ ሀገራትም የራሳቸውን ስትራቴጂ መቀየስና የምርታቸውን ጥራት በመጨመር ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

ቻይና በአረንጓዴ ልማት፣ በታዳሽ ኃይልና በኢንዱትሪ ዘርፎች በትኩረት እየሰራች ሲሆን በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስም(AI) ከምዕራባውያን ጋር የአንገት ላንገት ውድድር ውስጥ ከገባች ቆየት ብላለች።

ይህ እቅድ የቻይናን የልማት እቅድ ፍንትው አድርጎ ከማሳየት በተጨማሪ ለአለም “የአብረን እንደግ” ግብዣ ነው።

ቻይና በየአምስት አመቱ አዲስ የጊዜ  መርሃግብር ፋኖተ ካርታ የፕሮጀክቶችን  ዝርዝርና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎችን ታስቀምጣለች። ይህ የረጅም አመት እቅድ የሚወጣበት መንገድ አሳታፊ መሆኑ እቅዱ ተግባራዊና ተቀባይነት እንዲኖረው አስችሎታል። ዢ እንደተናገሩት እቅዱ የሚነደፈው ቢሮ ቁጭ ባሉ ባለስልጣናት ሳይሆን ከስራ አስኪያጆች፣ ከነጋዴዎች፣ ከምሁራንና ከተራ ዜጎች መረጃዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመሰብሰብ ነው። የተሰበሰበው መረጃ በናሽናል ፒፕልስ ኮንግረስ ከተገመገመ በኋላ የዋናው እቅድ ግብአት የሚሆንበት አስራር መኖሩ ለእቅዱ ጥንካሬ ወሳኝ ሆኗል።

በዚህ እቅድም 3 ሚሊዮን አስተያየቶች መሰብሰባቸውንና ከእነዚህ ውስጥ 1500 ሀሳቦች የእቅዱ አካል መደረጋቸውን አማካሪው ዢ ተናግረዋል። እቅዱን አሳታፊ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች እቅዱ በታለመለት ጊዜ ግቡን እንዲመታ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ቻይና አለምን በቴክኖሎጂ ለመምራት በእቅድ እየሰራች መሆኗን ያመላከተችው የ2026ቱን አዲስ አመት ባከበረችበት ወቅት ነበር። በአዲሱ አመት አከባበር ላይ የተደረጉ የሮቦት ትርኢቶች መላውአለምን ያስደመሙና ቻይና የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ መራቀቅ ግልጽ ያደረጉ ነበሩ

Share this article

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው