በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነትና የጸጥታ ቀውስ በዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ላይ በፈጠረው መስተጓጎል ምክንያት 167 ኮንቴይነር የደቡብ አፍሪካ የድንጋይ ፍራፍሬዎች (Stone Fruits) በባህር ላይ መታገዳቸው ተገለጸ።
በነዚህ ኮንቴይነሮች ውስጥ ወደ 675,000 ካርቶን የሚጠጉ የድንጋይ ፍራፍሬዎች (Stone fruits) እና 900,000 ካርቶን አፕልና ፒር (Apples and Pears) ይገኛሉ።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ግጭት መባባሱን ተከትሎ በርካታ የጭነት መርከቦች የተለመደውን የጉዞ መስመራቸውን እንዲቀይሩና ረጅም ርቀት እንዲጓዙ ተገደዋል። ይህ የጉዞ መስመር ለውጥ ፍራፍሬዎቹ መድረስ ከነበረባቸው ጊዜ በላይ በባህር ላይ እንዲቆዩ በማድረጉ ለአምራቾችና ላኪዎች ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል።

ደቡብ አፍሪካ በየዓመቱ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የምትልከው የፍራፍሬ ኤክስፖርት 1.3 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው ሲሆን አሁን የተከሰተው ጦርነት ከዚህ ኤክስፖርት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነውን አደጋ ላይ ጥሎታል። የድንጋይ ፍራፍሬዎች (እንደ ኮክ፣ ፕለምና አፕሪኮት ያሉ) በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ በመሆናቸው በባህር ላይ የሚፈጠር ጥቂት ቀናት መዘግየት እንኳ የምርቱን ጥራትና ዋጋ በእጅጉ ይጎዳዋል።
ይህ ክስተት በመካከለኛው ምስራቅ ያለው አለመረጋጋት ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ ያለውን የንግድ ሰንሰለት እንዴት እያመሰቃቀለው እንደሚገኝ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። ቀደም ሲል በሆርሙዝ ወሽመጥና በቀይ ባህር አካባቢ የነበረው ውጥረት በነዳጅ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ የሚታወቀ ሲሆን አሁን ደግሞ የግብርና ምርቶች ኤክስፖርት ላይ ጫና ማሳደር ጀምሯል።









