የአውሮፓ ህብረት በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ለኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረው የበጀት ድጋፍ ከ6 አመታት በኋላ መጀመሩ አስታውቋል።
ለሁለት አመታት የቆየው ጦርነት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና ህወሃት በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ በፈረሙት የዘላቂ ሰላም ስምምነት ከተቋጨ 3.5 አመት ሆኖታል።
በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮጵያ- አውሮፓ ህብረትና አፍሪካ ህብረት የቢዝነስ ስብሰባ ላይ የተገኙት የአውሮፓ ህብረት የአለም አቀፍ ትብብር ኮሚሸነር ጆዜፍ ሲከላ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ድጋፍ ወሳኝ በሆኑት የኃይል፣የግንኙነት፣ የግብርናና የጤና ዘርፎች ላይ መጀመሩን አስታውቀዋል።
ሲከላ “የእዚህ ቀን ትልቁ አዲስ ነገር የአውሮፓ ህብረት አቋርጦት የነበረውን የኢትዮጵያ ድጋፍ መጀመሩ ነው። እንደምታውቁት በሰሜን ኢትዮጵያ የተነሳውን ጦርነት ተከትሎ ድጋፉ እኤአ በ2020 ተቋርጦ ነበር” ብለዋል።
ኮሚሸነሩ የድጋፉ መጀመር የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ባለው ማሻሻያ እምነት እንዳደረበትና ለረጅም ጊዜ ግንኙነት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም እንዳሉት ኢትዮጵያና ህብረቱ ለሚያደርጉት የጋራ የዲጅታል ልማት 150 ሚሊዮን ዩሮ ተመድቧል።
የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለአግሪ-ፉድ ቢዝነስና ለአርሶ አደሮች ብድር የሚውል ከዘመን ባንክ ጋር የ20 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የገጠር ቤተሰቦችን በተለይም ሴቶችንና አነስተኛ የንግድ ተቋማትን በፋይናንስ ለመርዳት የሚውል የ110 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት መፈራረሙን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ትልቁ የገበያ መዳረሻ መሆኑንና በሁለቱ መካከል ያለው ንግድም ባለፈው አመት አዲስ ሪከርድ የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።













