በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያው የዘላቂ ሰላም ስምምነት(CoHA) እንዲደረስ የዋና አደራዳሪነት ሚና የተጫወቱት ኦሊሰጎን ኦባሳንጆ በዛሬው እለት ትግራይ ክልል መቀሌ መግባታቸውን በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው አስተዳደር አስታውቋል።
ኦባሳንጆ ወደ ትግራይ ጉዞ ያደረጉት የአፍሪካ ህብረት በቅርቡ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛ አድርጎ ከሾማቸው በኋላ ነው። ኦባሳንጆ ሁለት አመታት ያስቆጠረው ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት በተደጋጋሚ ወደ ትግራይ ተጉዘው የነበረ ሲሆን ጦርነቱ በስምምነት ከተቋጨ በኋላ ግን
ታህሳስ 20፣ 2015 ዓ.ም. የአፍሪካ ህብረት የክትትል፣ የማረጋገጫና ተገዢነት ተልዕኮን (AU Monitoring, Verification and Compliance Mission – AU-MVCM) በይፋ ስራ ለማስጀመር አቅንተው ነበር። ይህ የኦባሳንጆ ጉዞ ከስምምነቱ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
በትግራይ ክልል፣ የፌደራል መንግስትና ህወሓት በስምምነት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያቋቁሙ ተስማምተው ነበር።
ነገርግን ህወሓት ወደ ሁለት መከፈሉን ተከትሎ በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን አሁን ላይ ከጦርነቱ በፊት የነበረውን ምክርቤት ወደ ስልጣን በመመለስ የትግራይ ህጋዊ ወኪል መሆኑን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ እውቅና እንደማይሰጥ ገልጿል።ወደ ስራ የተመለሰው ምክር ቤት ከከጦርነቱ መቀስቀስ በፊት የነበሩትን ዶ/ር ደብረጽዮን በድጋሚ በፕሬዝዳንትነት እንዲሁም ሌሎችን አባሎችን በካቢኔ አባልነት መሾሙን ማስታወቁ ይታወሳል።
በፌደራል መንግስት እውቅና ያለውና በፕሬዝዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የእነ ዶ/ር ደብረጽዮንን ቡድን አካሄድ ወደ “ግጭት የሚያመራ” ነው በማለት በጽኑ ማውገዙ አውግዟል።
የኦሳንጆ ወደ ትግራይ መሄድ አሁንም ያላለቁና መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚገባ ጉዳዮች እንዳሉ የሚያመላክት ነው።









