የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚቼል (Mark Mitchell) በአዲስ አበባ በተካሄደው አህጉራዊ ሲምፖዚየም ላይ በተናገሩት ንግግር፣ በመገንባት ላይ ያለው አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ (Bishoftu International Airport) “በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ አህጉር በመካሄድ ላይ ያለ ትልቁ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት” መሆኑን በመግለጽ፣ ፕሮጀክቱ የዋሽንግተንን ሙሉ ትኩረትና ድጋፍ ማግኘቱን ይፋ አድርገዋል።
ማርክ ሚቼል በንግግራቸው ለቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ትኩረት የሰጠው የንግድ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (Department of State) እና የመከላከያ/ጦር ሚኒስቴር (Department of War/Defense) ጭምር ናቸው።
ይህ ዓይነቱ የተቀናጀ የአሜሪካ መዋቅሮች ጥረት የሚያሳየው፣ አሜሪካ ፕሮጀክቱን እንደ አንድ የሲቪል አቪዬሽን ግንባታ ብቻ ሳትመለከተው፣ በምስራቅ አፍሪካና በቀይ ባህር ቀጠና ያላትን ስልታዊ፣ የደህንነት እና የኢኮኖሚ የበላይነት ለማረጋገጥ እንደ ትልቅ ድልድይ እንደምትጠቀምበት ነው።
የቴክኖሎጂ እና የደህንነት የበላይነት
በመግለጫው ላይ አሜሪካ “እጅግ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና የተጠበቁ ቴክኖሎጂዎችን” ወደ ፕሮጀክቱ እንደምታመጣ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ቀዳሚውን አየር መንገድ (የኢትዮጵያ አየር መንገድ) የምታስተዳድር ሀገር እንደመሆኗ መጠን የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመቀበል አቅም መጣበቅ ትልቅ ፈተና ሆኖባት ቆይቷል።
አዲሱ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን የመላው አፍሪካ እና የዓለማችን ዋና የአቪዬሽን ማዕከል (Global Aviation Hub) የሚያደርጋት ሲሆን የአሜሪካ ኩባንያዎች ቀጥተኛ መኖሩ ደግሞ የፋይናንስ አቅርቦትን ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እና የፕሮጀክቱን ጥራት ከፍ እንደሚያደርገው ይታመናል።












