Loading...

ኢትዮጵያ በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ውሳኔ ሰጭነት “በጉልበቷ ታረጋግጣለች” — ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

Prime Minister Abiy Ahmed Ali speech as he was elected as chairperson of the party

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በድጋሚ ከተመረጡ በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር፣ ኢትዮጵያ በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን አቅሟን “በሰዎች ችሮታ ሳይሆን በጉልበቷ ታረጋግጣለች” ብለዋል።

7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ባሸነፈው የብልጽግና ፓርቲ በድጋሚ በመሪነት የተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን ንግግር ያሰሙት ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ግብጽ እና ሶማሊያ ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ ኢትዮጵያ ይመለከተኛል በምትለው የቀይ ባሕርና የአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ መክረው የጋራ መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ፣ በቀይ ባሕርና በአባይ ውሃ ዙሪያ የሚደረጉ ማናቸውም ውይይቶች የኢትዮጵያን ጥቅም ከግምት ያስገቡ ሊሆኑ እንደሚገባ በመግለጽ ለአራቱ ሀገራት መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል።ሀገራቱ ቀይ ባሕርን የማስተዳደር ጉዳይ የቀይ ባሕር ዳርቻ ሀገራት ብቻ ነው የሚል ይዘት ያለው መግለጫ ነው ያወጡት።

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና “አንከር ሀገር” መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የባሕር በርን ጨምሮ “ያጣቻቸውን ፍላጎቶች በራሷ መንገድ ታረጋግጣለች” ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በድርድር የቀይ ባሕር ተጋሪ ሀገር ለመሆን ያላትን ፍላጎት በይፋ ከገለጸች ወዲህ ከኤርትራ፣ ሶማሊያና ግብጽ በጎ ምላሽ አላገኘችም። ኢትዮጵያ ግን ቀይ ባሕር የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ የማትተወው አጀንዳ መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለጸች ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዛሬው ንግግራቸው የባሕር በርን አስፈላጊነት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
“ጎረቤቶቻችን የተፈጥሮ ወዳጆቻችን ናቸው። ስለሆነም ከሁሉም ጋር በሰላም፣ በጋራ ጥቅምና በትብብር የመሥራት መርሃችንን እንገልጻለን። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር እውን ሊሆን አይችልምና በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ ወጥታ መግባት የምትችልበት በር እንዲኖራት ተግተን እንሠራለን” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ጎረቤቶቻችን፣ የአፍሪካ ቀንድ፣ የባሕረ ሰላጤው ሀገራትና አውሮፓ በለውጥ ማዕበል እየተጎበኙ ነው” መሆኑን ጠቅሰው፣ የሀያላን ሀገራት መራኮቻ በሆነው የቀይ ባሕር ቀጠና የምትገኘውን ኢትዮጵያ መጎብኘቱ አይቀርም ብለዋል።
ስለሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ጂኦፖለቲካዊ ለውጥ ባመጣው ውጥንቅጥ ውስጥ አሸናፊ ለመሆን ጠንካራ ሆኖ መገኘት ይገባል።

በበርካታ ተግዳሮቶች የታጀበውን ምርጫ ማሸነፋቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ መንግሥታቸው ሊሠራቸው ያቀዳቸውን ተግባራትም ዘርዝረዋል። ከእነዚህም መካከል ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ፣ ሙስናን መዋጋት፣ የኢኮኖሚ ልማትን ማፋጠን፣ የመንግሥትን ተቋማዊ አቅም ማጠናከርና የኢትዮጵያን ቀጠናዊ ተጽዕኖ ማሳደግ ይገኙበታል።

Share this article

Subscribe

By pressing the Subscribe button, you confirm that you have read our Privacy Policy.
Your Ad Here
Ad Size: 336x280 px

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው